Ethiopia

ከሁለት ሳምንት በፊት ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ፍቃድ ውጭ ገብተዋል የተባሉ አርባ አምስት የፌደራል ፖሊስ ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል አባላት ከመቀሌ እንዲመለሱ ተደርገዋል

አባላቱ በአሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የመጡበት አላማም እስኪታወቅ ድረስ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ በፌደራል ካምፕ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጎ ነበር።

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ረዳኢ ኃለፎም ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ ችግር ባለመኖሩ የፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል አስፈላጊ አለመሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ጨምረውም ክልሉ ድጋፍ የሚጠይቀው ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ ነገር ሲያጋጥም ወይም በልዩ ሁኔታ ከተወሰነ መሆኑን ጠቅሰው “ሁለቱም ጉዳዮች እኛ ጋር የሉም” ብለዋል።

“ለተወሰኑ ቀናት የፌደራል ፖሊስ አባላት በካምፑ ውስጥ ቆይተዋል። ወደ ክልሉ የገቡበት መንገድ ችግር ነበረው። እኛ ባልጠየቅንበት እና በማናውቀው ጉዳይ ነው የመጡት” በማለት የፀረ-ሽብር ግብረ ኃይሉ ለምን መቀሌ እንደተገኘም ግልፅ እንዳልሆነም ተናግረዋል።

በወቅቱ የፌደራል ፖሊስና የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ረዳኢ ጉዳዩን መካዳቸው የሚታወስ ነው። የዚያ አይነት ምላሽ የተሰጠበት ምክንያት እንደነበረው አቶ ረዳኢ ይናገራሉ ።

“እውነት ነው ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተራ ወሬ ነው የሚል መልስ ስንሰጥ ቆይተናል። ምክንያቱም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከእውነት የራቀ መረጃ እየተሰራጨ ስለነበርና፤ ለትግራይ ህዝብ እና ለትግራይ መንግስት ብሎም ለስርአቱ ስለማይጠቅም የሚሰሩ ስራዎች ተሰርተው ወቅቱን ጠብቆ በትክክለኛ ጊዜ መነገር ስለነበረበት ነው” ብለዋል።

የፌደራል ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ከክልሉ መንግሥት ፍቃድ ውጭ መግባቱን አስመልክቶ ከፌደራል መንግሥት ጋር ቅራኔ ተፈጥሮ እንደሆነ አቶ ረዳኢን ቢቢሲ ጠይቋቸዋል።

“ከፌደራል መንግሥት ጋር የሚያቃቅር ነገር የለም። ለተልእኮ መጥተው ከሆነ ለዚያ የሚሆን ነገር የለም። አንድ ሃገር ከመሆናችን አንፃር ከመረዳዳት ውጭ ምንም ነገር የለም” ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ግብረ ኃይሉ እንዲወጣ ባዘዛው መሰረት ዛሬ ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ተገልጿል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button