Politics

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተፈጠረ ግጭት እስካሁን 39 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል። በሰውና ንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተፈጠረ ግጭት እስካሁን 39 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል። በሰውና ንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በአማራና ቅማንት ብሄረሰቦች መካከል በተቀሰቀሰና እስካሁን መብረድ ባልቻለ የስርበርስ ግጭት እስካሁን 39 ሺህ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መሰደዳቸውና በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።

የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የግጭቱ መንስዔ በወንድማማች ህዝቦች መካከል መቃቃር እንዲፈጠር ተግተው የሚሰሩ ሃይሎች ናቸው።

በዚህ ሴራ ሳቢያ በተፈጠረ መቃቃርና  ሆን ተብሎ በተቀናበረ የጸጥታ ችግር ምክንያት በተፈጠሩት ግጭቶች በበርካታ ሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

ግጭቱ እንደገና ያገረሸበትን ምክንያት አቶ አሰማኸኝ ሲናገሩ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም አካባቢውን ለማረጋጋት ተሰማርቶ የነበረው 24ኛ ክፍለ ጦር ከስፍራው ወጥቶ 33ኛ ክፍለ ጦር ለግዳጅ ሲገባ በአካባቢው  የተደራጁ ቡድኖች  በጸጥታ አካላት ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ነው  ።

በዚህ የተነሳ በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል ግጭት በመቀስቀሱ በርካታ መኖሪያ ቤቶች በእሳት የተቃጠሉ ሲሆን አያሌ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል ።

አማራና ቅማንት ሁለት ወንድማማች ህዝቦች መሆናቸው እየታወቀ ልዩነት በመፍጠር አካባቢውን የግጭት ቀጠና ለማድረግ  የሚሰሩ ሃይሎች አሉ ያሉት አቶ አሰማኸኝ በዚህ ሳቢያም ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደአቶ አሰማኸኝ ገለጻ እነዚህ ሃይሎች በሺዎች ሚቆጠሩ በርካታ ከባድ መሳሪያዎችን በህገ ወጥ መንገድ ወደስፍራው በማስገባት ለዚሁ እኩይ አላማ ላሰለጠኗቸው አካላት አስታጥቀዋል። በዚህም በንጹሃን ዜጎች ህይወት ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

እስካሁንም በምዕራብ ጎንደርና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት 39 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንም አቶ አሰማኸኝ አስረስ ተናግረዋል ።

ከግጭቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የገለጹት አቶ አሰማኸኝ ቀሪዎችም የእሥር ማዘዣ ወጥቶባቸው እተፈለጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልላዊ መንግስት በንፁጹሃን ዜጎች ላይ በደረሰው የህይወት መጥፋትና  ጉዳት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶታል ያሉት አቶ አሰማኸኝ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም  አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአካባቢው ያለውን አለመረጋጋት ወደ ነበረበት ለመመለስም  የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት  እየሰራ መሆኑን አቶ አሰማኸኝ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

 

 

 

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button