EthiopiaSportSports

የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮ አሸናፊው ልዑክ እና አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በቤተመንግስት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል

በዴንማርክ አርሁስ በተካሔደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከዓለም አንደኛ በመሆን ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የኢ.ፌ.ዴ. ሪ መንግስት የተለያዩ የገንዘብና የሰርተፊኬት ሽልማቶችን ትናንት ምሽት በቤተመንግስት አበርክቷል፡፡

በአገር አቋራጭ ውድድሩ ቡድኑ በ5 ወርቅ፣ 3 ብር እና 3 ነሃስ፣ በድምሩ በ11 ሜዳልያዎች ከዓለም ቀዳሚ ደረጃን በመያዝ ወደ ሀገሩ የተመለሰ ሲሆን በቤተ መንግስት በነበረው የእውቅና እና የማበረታቻ የሽልማት ስነ ስርዓት ከ1.4 ሚሊዮን ብር በላይ ለቡድኑ አባላት ተሰጥቷል።

የሪዮ ኦሊምፒክ በማራቶን የብር ሜዳልያ አሸናፊው አትሌት ፈይሣ ሌሊሣ በልዩ ሁኔታ፤ የስፖርት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ በጠ/ሚ/ሩ እና በፕሬዝዳንቷ አማካይነት የ500 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።

በዚሁ ስነ-ስርዓት ላይ ፕሬዝደነት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እንዳሉት ስፖርት የተለያዬ ዘር፣ ፖለቲካዊ አመለካከትና እምነት ያላቸው ሰዎች በአንድ ላይ አሰባስቦ በጨዋታው ህግና መርህ ብቻ እንዲመሩ የማድረግ ፀጋ አለው፡፡ ይህንን የስፖርት ልዩ ውበት ለሀገር ግንባታ እና ለህዝቦች አንድነት መጠቀም እንደሚገባም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ አትሌቶቹ ያስመዘገቡት ድል የመደመርን ፋይዳ በተግባር ያስመሰከረ ነው፤ እርስ በእርስ በጥሞና ተደማምጦ ተባብሮ በመሥራት፣ ትዕግሥትን ማዳበርና ጠንክሮ መሥራትን ውድድሩን ካሸነፉት አትሌቶች መማር ያለብን ዕሴቶች ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፤ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ስመጥርና ታዋቂ አትሌቶች፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የሚድያ አካላት ታድመዋል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button