EthiopiaPoliticsSocial

ጠ/ሚ ዶክተር አብይና ምክትል ጠ/ሚ አቶ ደመቀ ከሃገር መከላከያ የተለያየ ክፍለ ጦር ከተውጣጡ የጦር ሰራዊት አባላትጋር ተወያዩ

አርትስ 30/01/2011
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከሃገር መከላከያ የተለያየ ክፍለ ጦር ከተውጣጡ የጦር ሰራዊት አባላት ጋር ተወያይተዋል።

አባላቱ በነበራቸው ቆይታ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄ ማቅረባቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘይኑ ጀማል ለ ኤፍ.ቢ.ሲ ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራሉ አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን አግኝተው ጥያቄያቸውን በአካል ለማቅረብ ወደ ቤተ መንግስት ማምራታቸውንም ነው የተናገሩት።

በወቅቱም ሰላማዊ ውይይት ማድረጋቸውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለአባላቱ በዚህ መልኩ ወደ ቤተ መንግስት መምጣታቸው ስህተት መሆኑን ነግረዋቸው አባላቱም ስህተቱን ተቀብለዋል ነው ያሉት።

ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላም አባላቱ ፑሺ አፕ እንዲሰሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታዘዙ በኋላ የእራት ግብዣ እንደተደረገላቸውም ገልጸዋል።

ከዚህ ውጭ ግን ቤተ መንግስት አካባቢ የነበረው ሁኔታ ፍጹም ሰላማዊ መሆኑንም ኮሚሽነር ጀኔራሉ አስረድተዋል።

አባላቱ ከተጣለባቸው ሃገራዊ ሃላፊነት እና ግዳጅ ጋር ተያያዥ ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

በውይይቱ የመከላከያ አባላት እንደዜጋ ጥያቄያቸው ሊደመጥ እና በተግባር መመለስ እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጠቁመዋል።

መንግስት እንደሃገር የጀመረው የማሻሻያ ስራ በመከላከያ ዘርፉም በተመሳሳይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ተጨማሪ ውይይት በሚፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያ መድረኮች ይመቻቻሉ ያሉት አቶ ደመቀ፥ ጥያቄዎችም በቀጣይ መንግስት በጀመረው የለውጥ ጉዞ ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ አረጋግጠዋል።

የመከላከያ አባለቱም በውይይቱ ለተነሱ የዘርፉ ችግሮች በሰከነ አግባብ እንዲፈታ እና የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዳይደናቀፍ ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ዝግጁነታቸውን ማረጋገጣቸወን ነው ፅህፈት ቤቱ ያስታወቀው።

(Photo Credit: Office of Deputy Prime Minister)

 

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button