EthiopiaPolitics

ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጣሊያን የኢትዮጵያ ጥብቅ ወዳጅ ናት አሉ

አርትስ 02/02/2011

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ   በብሄራዊ  ቤተመንግስት የራት ግብዣ  አድርገዋል  ፡፡  ዶ/ር አብይ አህመድ  በመድረኩ ላይ  ባደረጉት ንግግር  ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጋር  ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል ፡፡ 

ዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያና ጣሊያን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፓለቲካ ዘርፍ ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራና  ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ 

በጣሊያን እና ኢትዮጵያ መካከል በኢንቨስትመንት ፣ ንግድ ፣ በመሰረተ ልማት  እንዲሁም ህገወጥ ስደትን በመከላከል ዙሪያ ያለውን ትስስር ለማጠናከር መስማማታቸውን ገልጸዋል ፡፡ 

ጣሊያን የኢትዮጵያ የልማት ትብብር ቀዳሚ አጋር ከሆኑ  ሀገራት መካካል አንዷ መሆኗን አንስተው ትብብሩ የበለጠ መጠናከር እንዳለበት  ዶ/ር አብይ አህመድ ተናግረዋል፡፡ 

ለቀጠናው ሰላምና ደህንነት  መረጋገጥ ጣሊያን ያላትን ድጋፍ አድንቀው ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል ፡፡ 

ጁሴፔ ኮንቴ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጣሊያን ታሪካዊና ሁለገብ ትስስር እንዳለቸው አውስተው ይህ ትብብርም ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር በቁርጠኝነት ለመስራት  ከዶ/ር አብይ አህመድ ጋር  ከመግባባት ላይ ደርሰናል  ብለዋል፡፡ 

 በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉትን የፓለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና ለውጡን የሚመራውን መንግሥት አድንቀው ጣሊያን የለውጡን እንቅስቃሴ  ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡ 

ጁሴፔ ኮንቴ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረውን የጦርነት ሁኔታ በአዲስ የሰላምና የወዳጅነት ምዕራፍ  መተካቱ  በሳል እርምጃ መሆኑንም  ተናግረዋል ፡፡ 

 የሰላም ሂደቱ ከሁለቱ ሀገራት አልፎ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት አዲስ በር የከፈተ መሆኑንም  ገልጸዋል ፡፡ ጣሊያን ለሰላም ሂደቱ መጎልበትና ዘላቂነት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን  አረጋግጠዋል ፡፡  

ኢትየጵያ  የአፍሪካ  ቀንድ  የሰላም መልህቅ ናትም ብለዋል ፡፡ 

ጁሴፔ ኮንቴ በሁለትዮሸና በባለብዙ ወገን መድረኮች ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል ፡፡ 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት እንዳለው ኢትዮጵያና ጣሊያን መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1889 ነው፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button