Breaking News

በማሻሻያ አዋጁ መሰረት እንደአዲስ የተዋቀሩትንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ የቀረቡት 19 የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ፀደቁ

በማሻሻያ አዋጁ መሰረት እንደአዲስ የተዋቀሩትንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ የቀረቡት 19 የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ፀደቁ

አርትስ 06/02/2011
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት እያካሄደ ባለው 2ኛ መደበኛ ስብሰባው የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም መንግስት ባለፉት ጥቂት ወራት ሲሰራው ከነበረው ሰላምን የማረጋገጥ ስራ በተጨማሪ ህዝቡ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁ፣ ህገ መንግስቱ እና የህግ የበላይነት እንዲከበር እና ከሌብነት የፀዳ አሰራር እንዲኖር ፍላጎቱ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የመንግስት ተቋማት በአዲስ መልክ እንዲደራጁ እንዲሁም የካቢኔ አባላትን ቁጥር ወደ 20 ዝቅ እንዲል መወሰኑን ተናግረዋል።
ረቂቅ አዋጁ የአስፈፃሚ አካላትን ማጠናከር እንደሚችልም የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቀጣይ እንደአዲስ የሚደራጁ አካላትንም ይፋ አድርገዋል።
በዚህ መሰረትም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤቶች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የምርጫ ቦርድ፣ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም እና ሌሎች ተቋማትም ራሳቸውን ፈትሸው እንደ አዲስ ከሚደራጁት ውስጥ ተመድበዋል።
ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቀረበውን ማብራሪያ ካደመጠ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡትን እጩ የካቢኔ አባላት ሹመት አጽድቆታል።
ከዚህ በማሻሻያ አዋጁ መሰረት በተጨማሪም እንደአዲስ የተዋቀሩትንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ የቀረቡትን 19ኝ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች አጽድቋል።
በዚህም መሰረት
1. የሰላም ሚኒስቴር
2. የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር
3. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
4. የገንዘብ ሚኒስቴር
5. ጠቅላይ አቃቤ ህግ
6. የግብርና ሚኒስቴር
7. የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
8. የገቢዎች ሚኒስቴር
9. የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
10. የትራንስፖርት ሚኒስቴር
11. የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር
12. የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር
13. የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር
14. የትምህርት ሚኒስቴር
15. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
16. የጤና ሚኒስቴር
17. የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር
18. ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
19. የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በማሻሻያ አዋጁ እንደአዲስ የተዋቀሩ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ሆነዋል።

በአዋጁ መሰረት ከአሁን በፊት የነበሩ እና ከዚህ በኋላ የማይቀጥሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ተለይተዋል። በዚህ መሰረትም
የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ሚኒስቴር – በሰላም ሚኒስቴር ስር የተጠቃለለ ሲሆን
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት – በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ተተክቷል።
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር – በሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ስር እንደአዲስ ተጠቃልሏል።
የንግድ ሚኒስቴር እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋህደው ንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ሆነዋል።
የከተማ እና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር ደግሞ ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር ተዋህዷል።

leave a reply