Social

በእንግሊዝ የጦርሃይል ሙዚየም የተቀመጠው የአጼ ቴዎድሮስ ጸጉር በነገው ዕለት ለኢትዮጵያ ይመለሳል

የአጼ ቴዎድሮስን ጸጉር ለማስመለስ ጥረት መካሄድ የጀመረው ከረጅም ጊዜ በፊት ቢሆንም በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻውል ከእንግሊዝ ብሄራዊ ሙዚየም ዳሬክተር ብርጋዴር ጀስቲን ማሴጄውስክ ጋር ከተወያዩ በኋላ በእንግሊዝ በኩል የአጼ ቴዎድሮስን ጉንጉን ለኢትዮጵያ ለመመለስ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የሁለቱ ሃገራት ሃላፊዎች በዚህ ቅርስ የመመለስ ሂደት ላይ የንጉሰ ነገስቱን ክብር በሚመጥን መልኩ በሚካሄደው የሽኝት ስነስርዓት ላይ በሰፊው መክረዋል፡፡ በሚካሄደው የሽኝት ስነስርዓቱ ላይም ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና መገኛኛ ብዙሃን እንዲገኙ ተጋብዘዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ልዑካን ቡድን ወደስፍራው የተጓዘ ሲሆን ቅርሱንም  እንደሚረከብ
ይጠበቃል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ታዋቂው የኢትዮጵያ ወዳጅና እንግሊዛዊ የታሪክ ባለሙያ የሆኑት ሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ይህ ውጤት ለኢትዮጵያ ታላቅ ድል ነው ብለዋል።

ታሪካዊ ዳራ

መጋቢት ወር 1860 ዓ.ም የእንግሊዝ መንግሥት በሮበርት ናፒየር የሚመራ ፣ በጊዜው እጅግ ግዙፍ የተባለ የጦር ኃይል አሰናድቶ አውሮፓውያን እስረኞችን ለማስፈታት ወደ ኢትዮጵያ ገባ።

መጋቢት 5 ቀን 1860 ዓ.ም ይህ ጦር ማዘዣውን በመቅደላ ምሽግ ላይ አድርጎ በተቀመጠው እና  በአመጽ በተዳከመው የንጉስ አጼ ቴዌድሮስ  ጦር ላይ ጥቃት ከፈተ።  በሁለተኛው ቀን ሚያዚያ 7 ከማለዳው ሦስት ሰዓት ላይ እንግሊዞች በመቅደላ ምሽግ ላይ የመጨረሻና  ከባድ  የሆነውን ጥቃት አደረሱ።

በውጊያው መሃል ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ቴዌድሮስ  እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም አላደርገውም  በማለት በአቋማቸው ፀኑ ፡፡ንጉስ አጼ ቴዌድሮስ  የሃይል ሚዛኑ ወደ እንግሊዞቹ ሙሉ በሙሉ እንዳጋደለ ስለተረዱ ለወታደሮቻቸው እንዲህ  በማለት ተለይተው ሄዱ “ተፈጽሟል! ከርሱ እጅ ከምወድቅ ብሞት ይሻለኛል”። ወዲያውኑ ከንግስት ቪክቶሪያ በስጦታ የተላከላቸውንና አዘውትረው ይይዙት  የነበረውን ሽጉጥ መዝዘው ወደራሳቸው በመተኮስ  በጀግንነት አለፉ።

በወቅቱ እንግሊዞቹ 9 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥተው ዘመቻውን ሲያቅዱ የመቅደላን ምሽግ አፍርሰው ንጉሱን ለመማረክ ነበር።  ሆኖም ምሽጉ ሲሰበር አጼ ቴዌድሮስ ሞተው ስላገኟቸው ጄኔራል ናፒየር እጅጉን ተናድዶ መቅደላ እንዲመዘበርና  አንዲዘረፍ ፣ የተረፈውም በእሳት እንዲጋይ አደረገ።

በወቅቱ የእንግሊዙ ጦር ከኢትዮጵያ ከዘረፋቸው ከ 500 በላይ የብራና መጽሃፍት ፣ የወርቅ የብር እና የነሃስ እቃዎች እንዲሁም የዘውድ አክሊሎች  በተጨማሪ አንድ ዛሬ ድረስ በእነግሊዝ የጦር ሃይል ሙዚየም ያስቀመጠውን ቅርስም አብሮ ይዞ ሄደ። የንጉስ አጼ ቴዌድሮስ ፀጉር ።

በቅርቡ በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የንጉሰ ነገስት አፄ ቴዎድሮስ ፀጉርን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ የቀረበውን ጥያቄ የለንደኑ  የጦር ሰራዊት ሙዚየም መቀበሉ ተነገሯል ፡፡በስምምነቱ መሰረትም  ሙዚየሙ  የአጼ ቴዌድሮስን ጉንጉን  ጸጉር ወደ ሀገሩ ለመመለስ በኢፌዲሪ የባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር ልዑካን ቡድን ቅርሱን ለመረከብ እንግሊዝ ሃገር ተገኝቷል።

በወቅቱ የእንግሊዝ ጦር ከኢትዮጵያ የዘረፈው ቅርስ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ይህንን ንብረት 14 ዝሆኖች እና 500 በቅሎዎች አስፈልገው ነበር።

 በእንግሊዚ የሚገኙ በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዲመለሱ  በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲን  ጨምሮ በርካታ ለሀገር ተቆርቋሪ ግለሰቦች የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ  ፀጉር ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ  በተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው  የሚታወቅ ሲሆን በዚህም ፀጉሩ ለህዝብ እየታ ቀርቦ ከነበረበት ሙዚየም እንዲነሳ ተደርጓል ይላሉ ዶክተር አሉላ።

እሳቸውን ጨምሮ አባታቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ብዙ ውጤትም አስገኝተዋል።  ዶክተር አሉላ እንደሚናገሩት ቅርሶቹን የማስመለሱ ሂደት ተጠናከሮ ይቀጥላል።  ከተለያዩ ሃገራት በግዢም ሆነ በዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተሰበሰቡትን የተዘረፉ ቅርሶች በአግባቡ መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሃለፊነት መሆኑንም አስምረውበታል።

 

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button