COVID-19

ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ከግንቦት ወር መጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መሰጠት ሊጀምር ነው፡፡

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ከግንቦት ወር መጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መሰጠት ሊጀምር ነው፡፡ በሶስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከ25 ሚሊዮን ዶዝ በላይ ለመከተብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ድጉማ በተለይ ሁለተኛው ዙር የኮቪድ-19 ዘመቻ እንደ ሀገር በርካታ ጠንካራ ጎኖች የታዩበት ነበር ብለዋል፡፡


በታህሳስ ወር ከተካሄደው የመጀመሪው ዙር ክትባት ጥሩ ተሞክሮዎችን በመውሰድ በሁለተኛው ዙር ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል፡፡ በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች ክትባቱን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት በጥንካሬ የተገመገሙ ሲሆን በመደበኛ ክትባት አሰጣጥ የተሻለ አፈጻጸም ቢኖርም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለይ በኩፍኝ ክትባት አሰጣጥ ላይ ክፍተት መታየቱ ተነግሯል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የእናቶች ህጻናት ጤናና ሥርዓተ ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ክትባቱን ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡ በዘጠኝ ወራቱ የዳይሬክቶሬቱ አፈጻጸምም የእናቶች እና ህጻናት ጤና፣ የአፍላ ወጣቶች እና የስነተዋልዶ
ጤና እንዲሁም የስርአተ ምግብ በተለይ የሰቆጣ ዲክላሬሽን ትግበራ በትኩረት ሲሰራበት እንደነበር ተናግረዋል።


የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ የክትባት ተደራሽነትን ለማስፋትና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማጉላት ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የጋራ ዕቅዶችን በማውጣት ጠንካራ የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው ገልፀው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
በኮቪድ 19 መከላከያ እና በመደበኛ ክትባቶች ዙሪያ በተካሄደ የግምገማ መድረክ የተገኙ የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና የአጋር ድርጅቶች ተወካዮችም ለ3ኛው ዙር የክትባት ዘመቻ ስኬትና የእናቶችና ህጻናት ጤናን ለማሻሻል የሚሰሩ ስራዎችን ለመደገፍ የድርሻውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button