AfricaEthiopiaPoliticsRegions

ኦነግ መንግስት የገባውን ቃል ያክብር ሲል አሳሰበ

አርትስ ታህሳስ 12 ቀን 2011

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት መንግስት የኦነግ ወታደሮችን አያያዝ በተመለከተ የገባውን ቃል እያከበረ ባለመሆኑ ሰራዊቱ ቅሬታ ገብቶታል።

ወደሃገር ውስጥ የገቡት የኦነግ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ከክልሉ ፖሊስ ወይም ከሃገር መከላከያ ልዩ ሃይል ጋር እንዲካተቱ ከፌዴራል መንግሰት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዳውድ ነገር ግን ስልጠናው ከወታደራዊ ተሃድሶ ይልቅ  በፓርቲ ፖለቲካ ላይ ማትኮሩ ወታደሮቹን ለተቃውሞ አነሳስቷቸዋል ብለዋል።

ማሰልጠኛ ለገቡት የኦነግ ታጣቂዎች ከሚቀርበው ምግብና ተገቢ አያያዝ እንዲሁም በስልጠና የሚቆዩበት ጊዜ በውል ካለመታወቁ ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች መቅረባቸውንና በመንግስት የተገባው ቃል እንዳልተፈጸመ ነው አቶ ዳውድ የገለጹት።

በተለይም ሰልጣኞቹ የኦነግ አመራሮች መጥተው ይጎብኙን በማለት ያቀረቡት ጥያቄም ምላሽ ስላልተሰጠው ወደምግብ ማቆም አድማ መግባታቸውን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።

ይህንን ተከትሎም በማሰልጠኛው ጠባቂዎች ተኩስ ተከፍቶባቸዋል ያሉት አቶ ዳውድ የሰልጣኞቹን በደል የሰሙት በኦሮሚያ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኙ የኦነግ አባላት እና ደጋፊዎች በአካባቢው የጸጥታ ችግር ፈጥረዋል ብለዋል። ይህ የጸጥታ ችግርም በአካባቢው እና በሃገሪቱ ሰላም ላይ ችግር ፈጥሯል ነው ያሉት።

መንግስት ይህንን  ተከትሎ በኦነግ አባላቶች ላይ እርምጃ መውሰድ እና ስም ማጥፋት መጀመሩ ድርጅታቸውን እንዳሳዘነው የተናገሩት ሊቀመንበሩ ይህ ከስምምነቱ ውጪ የሆነ ተግባር መቆም አለበት ነው ያሉት።

ኦነግ በተለይም በኦሮሚያ ክልል አደራጅነት ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ ከክልሉ ስልጣን ውጪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ጦርነት እንደማወጅ እንደሚቆጥረው ተናግረው እርምጃው ተገቢ አይደለም ብለዋል።

በመንግስት በኩል እየተካሄደ ያለው ስም ማጥፋት እንዲቆምና መንግስትም ስምምነቱን እንዲያከብር ያሳሰቡት አቶ ዳውድ በዛሬው ዕለት በኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ የተሰጠውን መግለጫም ፓርቲያቸው እንደማይቀበለው አስታውቀዋል።

ስለሆነም የተጀመረው ስም ማጥፋት ይቁም፣ መንግሰትም በሰልጣኞች ዙሪያ የገባውን ቃል ያክብር በማለት ነው የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ያሳሰቡት።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button