Breaking News

ፖምፒዮ የኢራንን ተፅዕኖ መቀነስ የሚያስችል ተልእኮ ይዘው መካከለኛው ምስራቅን እየጎበኙ ነው

ፖምፒዮ የኢራንን ተፅዕኖ መቀነስ የሚያስችል ተልእኮ ይዘው መካከለኛው ምስራቅን እየጎበኙ ነው፡፡

 

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ኢራን በመካለኛው ምስራቅ መረጋጋት እንዳይኖር ለፈፀመችው ተግባር ተጠያቂ ያደረጉት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባን ነው፡፡

ምክንያታቸው ደግሞ ኦባማ በቀጠናው ላለው አለመረጋጋት የኢራንን ሚና ቀላል  አድርገው መመልከታቸው ነው፡፡

ጉብኝታቸውን በዮርዳኖስ የጀመሩት ፖምፒዮ  በቀጣዩ ጉዟቸው ወደ ግብፅ ነው ያቀኑት፡፡   ካይሮ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የትራምፕ አስተዳር  በዚህ ጉዳይ አይቀልድም ብለዋል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው ፖምፒዮ በንግግራቸው ከአሜሪካ ይልቅ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ሚና አጉልተው ለማሳየት መሞከራቸው በሀገራቸው ሰዎች ዘንድ አስተችቷቸዋል፡፡

ጠላቶቻችንን ጊዜ በሰጠናቸው  ቁጥር እነሱ ይጠናከራሉ ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሁን ለኢራን ፋታ መስጠት አያስፈልግም የሚል መልእክት ነው ያስተላለፉት፡፡

ፖምፒዮ የባህረ ሰላጤ ሀገራት ጉብኝታቸውን በመቀጠል ወደ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት  አረብ ኤሜሬቶች፣ ባህሬን እና ኩዌት ያመራሉ፡፡

በዚህ ጉዟቸው አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ የምታራምደውን ፖሊሲ ከማስረዳት ባሻገር ከሀገራቱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነትን መመስረት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ፡፡

ኢራን የጋራ ጠላት በመሆኗ በተናጠል የሚደረግ ጥረት ውጤታማ አይሆንም ተባብረን ቴህራንን አቅም ማሳጣት ይኖርብናል የሚለው ሀሳብ  ዋነኛው የፖምፒዮ ትኩረት ነው ተብሏል፡፡

በተለይ ኢራን ትደግፋቸዋለች የተባሉት ሚሊሻዎች ከሶሪያ ምድር ሳይውሉ ሳያድሩ ተጠራርገው እንዲወጡ የጋራ ስራ ይጠብቀናል ነው ያሉት፡፡

 

 

 

leave a reply