Breaking News

የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ዋሽንግተን ሊያቀኑ ነው

የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ዋሽንግተን ሊያቀኑ ነው

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ እና የሰሜን ኮሪያው አቻቸው ኪም ዮንግ ኮል ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው ወደ ዋሽንግተን ከሚጓዙት የፒዮንግያንግ  ባለስልጣናት መካከል ከአሜሪካ ጋር የኮሪያን ልሳነ ምድር ከኒውክሌር ስጋት ነፃ ለማድረግ የሚደራደሩት ይገኙበታል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማቶች በዚህ መልክ ተገናኝተው መነጋገራቸው ኪም እና ትራምፕ በቀጣዩ ጊዜ ሊያደርጉት ስላሰቡት ሁለተኛ ዙር ድርድር መንገድ ይጠርጋል ተብሎለታል፡፡

ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን በአዲሱ ዓመት ዋዜማ  አሜሪካ በኛ ላይ የተጣለችውን ማእቀብ የማታነሳ ከሆነ የተለየ መንገድ እንከተላለን ማለታቸው በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ውጥረት ያባብሰዋል ተብሎ ተሰግቶ ነበር፡፡

ትራምፕ እና ኪም ሲንጋፖር ላይ ተገናኝተው የተገባቡትን ቃል በመተግበር በኩል የታየው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም እየተባሉ ይተቻሉ፡፡

እንዲያም ሆኖ አሁን ላይ መሪዎቹ እንደገና ተገናኝተው  ተጨማሪ ውይይት ለማካሄድ የሚያደርጉት ዝግጅት ምናልባት ካለፈው የተሻለ ውጤት ያስገኛል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

የሁለቱ መሪዎች ዳግም የመገናኘት ሀሳብ ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን በአዲሱ ዓመት ያደረጉት ንግግር ነገሩ እንደ አዲስ እንዲያንሰራራ አድርጎታል ነው የተባለው፡፡

 

leave a reply