Regions

አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው የ14 ቀን ቀጠሮ ተሰጣቸው

አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው የ14 ቀን ቀጠሮ ተሰጣቸው፡፡ ጉዳዩ በአዲስ አበባ እንዲታይና ዋስትና እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄም ውድቅ ሆኗል፡፡

አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ በተጠረጠሩበት የጥረት ኮርፖሬት የሀብት ብክነት ጉዳይ ዛሬ በባሕር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ በውጭ ሆነው እንዲከራከሩና ጉዳዩ አዲስ አበባ እንዲታይላቸውም ጠይቀዋል፡፡ በምክንያትነት ደግሞ የጤና ችግርና የቤተሰብን ድጋፍ በቅርበት ለማግኘት በሚል አቅርበዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ‹‹ተመዘበረ›› ካለው የሀብት መጠን ከፍተኛነት አንጻር ዋስትና እንዳይሰጣቸውና እንዲሁም የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈጸመው በአማራ ክልል በመሆኑ ጉዳያቸው በባሕር ዳር እንዲታይ ለፍርድ ቤቱ ጠይቋል፡፡ ምሥክሮችን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ስለሚያቀርብም የጉዳዩን በባሕር ዳር መታዬት ተገቢነት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ የዋስትና መብታቸውን ከልክሎ በጥብቅ ጥበቃ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ወስኗል፡፡ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ዋስትና የከለከለው ፍርድ ቤቱ የተመዘበረው ሀብት በአማራ ክልል ስለሆነ ጉዳዩ መታዬት ያለበት በባሕር ዳር እንደሆነም ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

በጥብቅ ጥበቃ እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ የወሰነው ከነበራቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት አንጻር መሆኑንም ችሎቱ አስታውቋል፡፡

የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ አጠናክሮ እንዲያቀርብ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ የዛሬ ውሎውን ችሎቱ አጠናቅቋል፡፡

አማራ ማስሚዲያ

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button