Economy

በደቡብ ክልል ዘጠኝ ሆስፒታሎች መገንባት የሚችል ገቢ ሳይሰበሰብ ቀርቷል ተባለ

በደቡብ ክልል ዘጠኝ ሆስፒታሎች መገንባት የሚችል ገቢ ሳይሰበሰብ ቀርቷል ተባለ።

በክልላዊ የታክስ ንቅናቄ ዙሪያ በሃዋሳ ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተወጣጡ የክልሉ ነዋሪዎች ጋር ምክክር በተካሄደበት ወቅት የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ አስረስ እንደተናገሩት የክልሉ ያለፉት ሁለት ዓመታት የተሰበሰበው የታክስ ገቢ መሰብሰብ ከሚገባው አንፃር ሲታይ 9 ደረጃቸውን የጠበቁ ዲስትሪክት ሆስፒታሎችን መገንባት የሚያስችል ገቢ ሳይሰበሰብ ቀርቷል ብለዋል።

ይህ ሳይሰበሰብ የቀረ ገቢ 113 ባለ አምስት ወለል የመማሪያ ህንጻዎች መገንባት ያስችል እንደነበር ወይም ከ104 ኪ.ሜትር በላይ አስፋልት ለመገንባት የሚያስችል ገንዘብ መባከኑ በጥናት መረጋገጡ ቁጭት ይፈጥራል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

በተያያዘ ዜና በሐዋሳ እና አካባቢዋ የሞተር ሳይክል ኮንትሮባንድ ወንጀል እየተስፋፋ መሆኑ ተገልጿል።

በደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል የሞተር ሳይክል ኮንትሮባንድ እየተስፋፋ በመሆኑ በሀገር ገቢ ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት ባሻገር የዜጎች ህይወት ላይ አደጋ እያደረሰ ነው ተብሏል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የሐዋሳ አካባቢ ኬላ ፈታሾችን ጠቅሶ እንደገለጸው በክልሉ በርካታ ሞተር ሳይክሎች ሞያሌን እና ያቤሎን በማቋረጥ ህገወጥ በሆነ መንገድ ወደ ዲላ እና ይርጋለም እንዲሁም ሐዋሳ እየገቡ ይገኛሉ፡፡

ሞተር ሳይክሎቹ አንድም እየተነዱ የሚገቡ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተፈታተውና በማዳበሪያ ተጠቅልለው ከሌላ ዕቃ ጋር በመደባለቅ ይገባሉ፡፡

ሞተር ሳይክሎቹ በተገቢው የዕቃ አወጣጥ ሂደት አልፈው የሚመጡ ባለመሆናቸውም በቀጥታ ከተሞች ውስጥ በመግባት ያለ ታርጋ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ተደርሶበታል ብሏል ሚኒስቴሩ።

በዚህም ያለመንጃ ፍቃድ በሚያሽከረከሩ ሞተር ሳይክሎች የተነሳ የበርካታ ዜጎች ህይወት እየተቀጠፈ እንደሚገኝና ችግሩን ለመቅረፍ በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት ህብረተሰቡ በባለቤትነት ሊያግዝ እንደሚገባም ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

 

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button