Uncategorized

የቦይንግ የአክሲዮን ዋጋ የ13 በመቶ ቅናሽ አሳየ

የቦይንግ የአክሲዮን ዋጋ የ13 በመቶ ቅናሽ አሳየ

በርከት ያሉ አየር መንገዶች ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙ አውሮፕላኖችን ከበረራ አገልግሎት እያስወጡ መሆኑም  ተገልጿል።

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን 157 ተሳፋሪዎችን ይዞ በቢሾፍቱ አቅራቢያ መከስከሱን ተከትሎ  የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቻይና የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖች በጊዜያዊነት ከበረራ ማገዳቸው ይታወቃል።

ከኢትዮጵያ እና ቻይና በተጨማሪም በርከት ያሉ አየር መንገዶች እና የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣናት ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙ አውሮፕላኖችን ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ ውሳኔ እያሳለፉ ነው።

የኢንዶኔዢያ የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙ አውሮፕላኖች በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ ትእዛዝ ማሳለፉ ነው የተነገረው።

ካይመን የአየር መንገድ እና ኮንኤይር የተባሉ የአየር መንገዶችም ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቻቸውን ከበረራ አገልግሎት አስወጥተዋል፡፡

በተጨማሪም የሲንጋፖር የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንም በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖች ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም አቀፍ በረራዎች በጊዜያዊነት አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ውሳኔ አስተላልፏል።

ባሳለፍነው እሁድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በርከት ያሉ የአር መንገዶች ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖች መጠቀምን በጊዜያዊነት ከማቆማቸው ጋር በተያያዘ ነው  የቦይንግ ኩባንያ የአክስዮን ዋጋ ቅናሽ ያሳየው፡፡

በዚህም በትናንትናው እለት የቦይንግ የአክሲዮን ዋጋ በ13 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በርግጥ በዘርፉ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች የአደጋው መንስዔ ባልታወቀበት ሁኔታ እርምጃው የፈጠነ ነው ቢሉም ገበያውን በቅርቡ የተቀላቀለው አዲሱ የቦይንግ አውሮፕላን ግን ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ መከስከሱ ኩባኒያው ላይ በርካታ  ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡

አዲሱ የቦይንግ ምርት አውሮፕላን ከሚነሱበት ጥያቄዎች መካከልም ከሶፍትዌር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ዋነኛው ነው ።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ቁመቱ 39 ነጥብ 52 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፥ ወደ ጎን ያለው ስፋት ደግሞ 35 ነጥብ 9 ሜትር ነው። ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በጠቅላላ 210 መቀመጫዎችን እንዳሉት መረጃዎች ያመለክታሉ።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button