Ethiopia

መረጃዎች የአውሮፕላን አደጋውን መንስኤ በተመለከተ ወደ ቦይንግ እየጠቆሙ ነው

መረጃዎች የአውሮፕላን አደጋውን መንስኤ በተመለከተ ወደ ቦይንግ እየጠቆሙ ነው። ብዙ ተስፋ የተጣለበት እና ለምርመራ ወደ ፈረንሳይ የተላከው የመረጃ ሳጥንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ከኢንዶኔዢያው ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው የሚያሣይ መረጃ አቀብሏል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት ከሆነውና ቢሾፍቱ አቅራቢያ ከወደቀው ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን ስብርባሪ ውስጥ የመረጃ መዝጋቢ ሳጥን(ብላክ ቦክስ) መገኘቱ የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ ሲቃትቱ ለነበሩ ልቦች ሁሉ እፎይታን አስገኝቷል።

ይህ ሳጥን በዚህ ፍጥነት ሊገኝ መቻሉ  በአደጋው  ዙሪያ የሚሰነዘሩ መላምታዊ መረጃዎችን በማስቀረት ሳይንሳዊ ምላሽ ለመስጠትም ብቸኛው ምንጭ ነው ይላሉ የአቪየሽን ባለሙያዌች።

የመረጃ ሳጥኑ ወደፈረንሳይ ለምርመራ ከተላከ በኋላ መላው አለም የምርመራውን ውጤት በጉጉት እየጠበቀ ቆይቷል።

ምንም እንኳን ሙሉ የአደጋው መንስዔ ይኼ ነው የሚባልበት ሙሉ መረጃ ገና ይፋ ያልተደረገ ቢሆንም አንዳንድ መረጃዎች ግን የአደጋው መንስዔ በቦይንግ አምራች ኩባንያ አውሮፕላኑ ላይ የተገጠመውና ለአብራሪዎች በቂ ስልጠና ያልተሰጠበት የኮምፒውተር ሶፍትዌር መሆኑ እየተገለጸ፣  ጣቶችም ወደቦይንግ ኩባንያ እየጠቆሙ ነው።

በዚህ መካከል የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የብዙዎቸ የአደጋ መንስዔ ግምት የሆነውን የሶፍትዌር ችግር የሚያጠናክር መግለጫ ሰጥቷል። የትራንስፖርት ሚኒስትሯ  ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስን ከሮይተርስ እና ሌሎች የሃገር ውስጥ መገናኛ በዙሃን ጋር በነበራቸው ቆይታ አደጋ ከደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የተገኘው የበረራ መረጃ  ባለፈው ጥቅምት ወር በኢንዶኔዢያ ባሕር ላይ ከወደቀው አውሮፕላን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው የሚያመለክት ነው ብለዋል።

አደጋው የገጠማቸው ሁለቱም  አውሮፕላኖች ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት የተባሉት የቦይንግ ኩባኒያ አዳዲስ ምርቶች ሲሆኑ በደረሰባቸው አሰቃቂ አደጋ በውስጣቸው የነበሩ የሁሉም ተጓዦች ህይወት አልፏል።

የበረራ መረጃ መዝጋቢ ሳጥኑ በከፊል ተጎድቷል የሚለው አንዳንድ ዜና ስለአደጋው በቂ መረጃ ላይገኝ ይችላል የሚለውን ስጋት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ መግለጫ ውድቅ አድርጎታል።

ሚኒስትሯ እንደተናገሩት ሙሉ መረጃው ከአውሮፕላኑ የመረጃ ማስቀመጫ ክፍል ላይ በስኬት ተገልብጧል።

የፈረንሳይ የአየር ትራንስፖርት ደህንነት መርማሪዎች የአውሮፕላኑን የበረራ መረጃ መመዝገቢያንና የበረራ ክፍል የድምጽ መቅጃን በመመርመር ያገኙትን ምርመራውን ለሚያከናውኑት የኢትዮጵያ ባለሙያዎች አስረክበዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራው ውጤት በ30 ቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚሆንም  ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ከተሰበሰበው መረጃ መነሻም “በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ ከወራት በፊት በኢንዶኔዢያው ተመሳሳይ አውሮፕላን ላይ ከደረሰው አደጋ ጋር ግልፅ መመሳሰል ታይቷል” ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የበረራ መመዝገቢያ መረጃዎቹ እንደሚያመለክቱት በሁለቱም የአውሮፕላን አደጋዎች ላይ ድንገተኛ የከፍታ መለዋወጥ እንደታየ፤ ይህም አውሮፕላኖቹ ያልተጠበቀ ከፍና ዝቅ የማለት ተመሳሳይ አጋጣሚዎች እንደተስተዋለባቸው ነው።

የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዴኒስ ሙሊንበርግ በበኩላቸው ድርጅታቸው በአውሮፕላን አደጋው ዙሪያ በሚደረጉ ምርመራዎች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል ብለዋል።

ሥራ አስፈጻሚው ጨምረውም በአውሮፕላኑ ውስጥ ያለውን የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት የሚመራውን ሶፍትዌር ለማሻሻል እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

በአየር ሁኔታ ምክንያት ዕይታን የሚያስቸግር ነገር አልነበረም የሚለው የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴን የሚከታተለው ፍላይት ራዳር 24 “አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ ወደላይ የወጣበት ፍጥነት የተረጋጋ አልነበረም” ብሏል።

አደጋው በተከሰተበት ስፍራ ነበርኩ ያለ የዓይን እማኝ አውሮፕላኑ መሬት ላይ ሲወድቅ ከባድ እሳት ተፈጥሮ ነበር ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጥቅምት 19ቀን 2011 ዓ.ም የኢንዶኔዢያ ላየን ኤር በረራ 610 ከኢንዶኔዢያዋ መዲና ጃካርታ ከተነሳ በኋላ በመከስከሱ የ189 ሰዎች ህይወት ማለፉ አይዘነጋም።

በወቅቱ የአደጋ መርማሪዎች እንደደረሱበት አውሮፕላኑ ሽቅብ በጣም ከፍ ወዳለ አቅጣጫ እንዳይወጣ የሚቆጣጠረው የአውሮፕላኑ ሥርዓት ላይ ችግር እንደነበረበት አመልክተዋል።

በዚህም ሳቢያ በረራው ወቅት የመቆጣጠሪያ ሥርዓቱ በተደጋጋሚ አውሮፕላኑን ወደታች እንዲያዘቀዝቅ ያደርገው ነበር ተብሏል።

የአውሮፕላኑ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ወደታች እንዲያዘቀዝቁ ከማድረጉ በፊት አብራሪዎቹ ይህንን ችግር የአውሮፕላኑን አፍንጫ ወደላይ ከፍ በማድረግ ለማስተካከል ጥረት አድርገዋል። ይህም በዘህ አዲስ የአውሮፕላን ምርት ላይ  ከሃያ ጊዜ በላይ እንደተከሰተ ተገልጿል።

ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ቢሾፍቱ ከተከሰከሰው አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን ብላክ ቦክስ  የወጣው መረጃ ፓይለቶቹ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ሲታገሉ እንደነበር ያትታል፡፡

ከመንደርደር (ቴክኦፍ) ጀምሮ ያቺ 6 ደቂቃ አብራሪዎቹ በከፍተኛ ደረጃ ሲታገሉ እንደነበረ  እና አውሮፕላኑ ገና ተንደርድሮ የመነሳት (ቴክ ኦፍ) ምዕራፍም ስላላጠናቀቀ ዋና አብራሪው እና ረዳቱ እጅግ ፈታኝ ትግል ሲያደርጉ እንደነበረ መቅረጸ ድምፁ አስቀርቷል ይላል የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ፡፡

የኢንዶኔዢያው አውሮፕላን ከተከሰከሰ ከወራት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ያሉ አየር መንገዶች ያሏቸውን ቦይንግ ማክስ ኤይት አውሮፕላኖችን ከበረራ ውጪ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

የቦይንግ ኩባኒያ እና የአሜሪካ የአቬሽን ባለስልጣንም እገዳዎቹን ሲቃወሙ ቆይተው ኋላላይ ምርቶቹ ዳግም ሊታዩ ይገባል ብለው እገዳውን መቀላቀላቸው ይታወቃል፡፡

የዚህ ሁሉ ምርመራ ውጤት  በአሁኑ ወቅት የዚህ አደጋ ምክንያት ያለምንም ተጨማሪ ግምት ሙሉ በሙሉ ወደቦይን ኩባንያ እንዲያነጣጥር አድርጎታል። ቦይንግ ኩባንያም ይህንን ተቀብሎ ውጤቱን በተስፋ መጠባበቅን የመረጠ መስሏል።ለዚህም ይመስላል በአደጋው ምርመራ ላይ አስፈላጊ ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀቱን ያስታወቀው።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button