SportSports

ባርሴሎና በሜሲ ልዩነት ፈጣሪነት ሊቨርፑልን አሸነፈ

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ግጥሚያ በካምፕ ኑ ላይ በባርሴሎና እና ሊቨርፑል መካከል ተካሂዶ በካታላኑ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡

የምሽቱን ጨዋታ ባርሳ 3 ለ 0 ሲረታ፤ ሊዮኔል ሜሲ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ቀሪዋን ደግሞ የቀድሞው የቀያዮቹ ተጫዋች ሊዩስ ሱዋሬዝ ከመረብ ጋር አገናኝቷል፡፡

የየርገን ክሎፕ ልጆች በምሽቱ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው እንዲሁም ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ከመሸነፍ አልዳኑም፤ ያገኟቸውን መልካም የግብ ዕድሎችን ወደ ጎልነት ቀይረው አለመውጣታቸው የመልሱን ጨዋታ ለመቀልበስ አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል፡፡     

የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ እና ኮከብ ተጫዋች ሜሲ በሊቨርፑል መረብ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጎል ሲያሳርፍ፤ በባርሴሎና መለያ የ14 ዓመት አገልግሎት 600ኛ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል፡፡ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ደግሞ የእንግዝ ቡድኖች ላይ ያስቆጠራቸውን የግብ መጠን 26 አድርሷል፡፡

የዘንድሮውን የቻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪንትም አርጀንቲናዊው ኮከብ በ12 ጎሎች እየመራ ይገኛል፡፡

የካታላኑ ባርሴሎና እንደ ክለብ በቻምፒዮንስ ሊጉ ታሪክ 502 ጎሎችን በተቃራኒ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል፤ ሪያል ማድሪድ 551 ግቦችን በመያዝ ቀዳሚው ክለብ ነው፡፡

ቡድኑ ከቀናት በፊት የሊጉን ውድድር ዋንጫ አስቀድሞ ለ26ኛ ጊዜ ማንሳቱ ይታወቃል፡፡

የመልሱ ጨዋታ ቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ አንፊልድ ሮድ ላይ ይከናወናል፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button