EthiopiaSocial

በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር እና ፍትህ እንዲሰፍን መደራጀት  ወሳኝ ነዉ ተባለ፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር እና ፍትህ እንዲሰፍን መደራጀት  ወሳኝ ነዉ ተባለ፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትና አስተዳደር ለማሻሻል በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያም ውይይት ተካሄዷል

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትና አስተዳደር በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡

የምክክር መድረኩ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራቾች የአሠሪና ሠራተኛ ሕግን በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግና እየተሻሻለ ባለው የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ላይ አጠቃላይ ምልከታ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡

የሠራተኛኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ለዜጎች ምቹ የስራ እድል በመፍጠር ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ መንግስት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ምቹ የሥራ ሁኔታን በመፍጠር ሂደት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከባለ ሀብቶች ጋር በጋራ ችግሮችን በመፍታት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ የግሉ ዘርፍ ለሀገር እድገት እንደ ኃይል የሚታይ የልማት አጋር በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ እየፈቱ ለመሄድ የሁለትዮሽ እና የሦሥትዮሽ መድረኮችን በመፍጠር በጋራና በጥምረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም እየተከለሰ ባለው የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ የሠራተኛው እና የአሠሪው ጥቅምና መብት እንዲከበት የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሠራተኛው መብትና ደህንነት እንዲጠበቅ እና ዝቅጠኛ የደመወዝ ወለል መወሰን የሚያስችሉ ጉዳዮች መካተታቸውን ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በበኩላቸው የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ የሠራተኛውን መብት ባስጠበቀና የሀገሪቱን ለኢንቨስትመንት ተመራጭነት ባልጎዳ መልኩ ማሻሻያ እንደተደረገበት ተናግረዋል፡፡ ሕጉ ዝቅተኛ የደሞዝ መጠን በድርድርና በግልፅ የማስቀመጥ እድል እንደሚሰጥም አክለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአሠሪና ሠራተኛ ሕግና አስተዳደር በተመለከተ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሠላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክትር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ገብሩ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር እና ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን መደራጀት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የአሠሪዎችና ሠራተኞች ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የኢንዱስትሩ ሠላምን ለማስፈን እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ምቹ የሥራ ሁኔታን ለመፍጠር መንግስት የአሠሪና ሠራተኛ ህጉን በማሻሻል ላይ ሲሆን ረቂቅ ሕጉ በሚኒስትሮች ምክርቤት ፀድቆ ለተጨማሪ እይታ ወደ ሚመለከተው የሕግ ክፍል መመራቱ ታውቋል፡፡

 

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button