EthiopiaPolitics

ጠ/ሚ ዶክተር አብይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ስለሀገራቸውና ስለ ወገናቸው እንዲያስቡ ጥሪ አቀረቡ

ጠ/ሚ ዶክተር አብይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ስለሀገራቸውና ስለ ወገናቸው እንዲያስቡ ጥሪ አቀረቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች፣ ብርቱና ጀግና ሕዝብ ያላት፣ ውብና ድንቅ ባሕሎችን ያቀፈች፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለዘመናት በፍቅርና በመግባባት የኖሩባት እንዲሁም የበርካታ ተፈጥሯዊ መስህብ ባለቤት ናት ብለዋል፡፡

ይሁን እንጅ ድህነት፣ የሕክምና አገልግሎት እጥረት፣ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እጥረት፣ ንጹሕ ውኃ አቅርቦትና የመንገድ አቅርቦት ችግር ከዚህ አኩሪ ታሪክ ጋር የማይመጣጠን ፈተና መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለጣቢያችን በላከው መግለጫ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ታዳጊዎች ስለሀገራቸውና ስለ ወገናቸው እንዲያስቡ ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቅሷል።

ለህጻናት ተማሪዎች መጻህፍት፣ የመጫወቻ ሜዳዎች እንዲሁም የመማሪያ ኮምፒውተሮች ዛሬም ብርቆች ናቸዉ ብለዋል።

ከዘመናት በፊት የነበሩት ጥቅጥቅ ደኖች ተራቁተው አዕዋፍና አራዊት ከየአካባቢው እየራቁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እርስ በርስ መጣላት፣ መገፋፋት፣ በዘር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ተለያይቶ መጋጨት፣ በየሚዲያው ጥላቻና ስድብን ማሠራጨት፣ መፈናቀልና ስደት የዘመናችን አስከፊ ገጽታዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዉን ስልጡን፣ ባለጸጋ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ማድረግ የሚቻለው በመተባበር በመሆኑ፥ የነገ ሃገር ተረካቢዎች ነገን እያሰባችሁ መሥራት አለባችሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

ከዚህ አንጻርም በውጭ ሃገር የሚገኙ ወጣቶችና ታዳጊዎች የዛሬውን ችግርና መከራ ሳይሆን የነገውን ተስፋ መመልከት፣ በሀገራቸው ተስፋ እንዳይቆርጡና ሁኔታውን መለወጥ፣ እንደሚቻልና ታሪክም እንሰራለን ብለው እንዲያምኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በተጨማሪም ስለሀገራቸውና ስለሕዝባቸው መልካም ነገር እንዲናገሩና እንዲመሰክሩ፣ ለሚጓዙበት ጎዳና እንጂ ለሚያጋጥማቸው ዕንቅፋት ሳይጨነቁ በመንገዳቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዕውቀትን ወደ ሀገራቸው በማሸጋገርና አዳዲስ አሠራሮችን በማምጣት እንዲሁም መጻሕፍትንና ኮምፒውተሮችን በማሰባሰብ፣ የብዙ ተማሪዎችን ሕይወት ማሻሻል እንደሚቻልም በመልዕክታቸው አንስተዋል።

እንዲሁም በየትምህርት ቤቶቹ በመግባት የበጎ ፈቃድ መምህር እንዲሆኑ፣ የማከማቻ ቋቶችን (ሰርቨር) በማዘጋጀት ዲጂታል መጻሕፍትን ተማሪዎች በስልኮቻቸው እንዲያገኙ ማድረግ እና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን አሰባስበው ለየትምህርት ቤቶች እንዲያደርሱም አደራ ብለዋል።

መጻሕፍትን በማሰባሰብ በታናናሽ ከተሞችና ትምህርት ቤቶች አብያተ መጻሕፍትን ማስፋፋት፣ ከሻይና ቡና በሚቀነስ ገንዘብ፣ በአካባቢ ቁሳቁስ የመጻሕፍት ቤቶችን መሥራትም የወጣቶችና ታዳጊዎች ተግባር ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

መጻሕፍቱን ደግሞ ከየቦታው መለቃቀምና በእርዳታ ማግኘት ትችላላችሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በቀላል ቴክኖሎጂዎች አብያተ መጻሕፍቱን ዲጂታል ማድረግ እንደሚቻልም አውስተዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የሠለጠነ አሠራርን በሀገሪቱ ማስለመድ፣ በሆቴሎች፣ በመሥሪያ ቤቶች፣ በግል ድርጅቶች፣ በገበያ አዳራሾች፣ በሆስፒታሎች፣ አገልግሎት በመስጠት የተሻለ አሠራርን ለሌሎች ማሳየትና ሀገሪቱ እንድትሆን የሚፈልጉትን ወጣቶቹ አድርገው ማሳየት እንዳለባቸውም አስታውሰዋል።

ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ለሕዝቡ ማበርከት ስለሚችሉት አስተዋጽዖ፣ ችግሮችን ቀርፈው፣ ፈተናዎችን አልፈው እንዴት ሀገር መገንባት እንደሚቻል የሚመክሩባቸው የወጣቶች የሐሳብ መለዋወጫ መድረኮችን በማዘጋጀትም ወጣቶች ራሳቸው ተነጋግረውና መክረው የመፍትሔ ሐሳቦችን ማምጣት ይገባቸዋልም ብለዋል።

የመኖሪያ ሥፍራችን ብዙ ያለን ሀገር ግን አንድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የትም ብትወለዱ ኢትዮጵያ በደማችሁ ውስጥ አለች፤ የአንዲት ሀገር ታላቅነት የሚወሰነውም በተተኪው ትውልድ ታላቅነት ነው ሲሉም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

እናንተ ከበረታችሁ፣ ተስፋ ካልቆረጣችሁ፣ ሀገራችሁን ለመለወጥ ከተነሣችሁ፣ የኢትዮጵያ ትንሣኤ እንደሚቀርብ አትጠራጠሩም ብለዋል፤ ወጣቶች ለአፍራሽ ወሬና አሉባልታ ቦታ እንዳይሰጡ በማስታወስ።

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለወጣቶቹ ስለሚነሣው አቧራ ሳይሆን ስለምናሳርፈው አሻራ እናስብ፤ የነገው ትውልድ በእናንተ እንዲኮራ፣ ስማችሁም ከሀገራችሁ ክብርና ገናናነት ጋር አብሮ እንዲጠራ ኑ አብረን አሻራ እናትም  ሲሉ ለወጣቶቹ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

ምንጭ፤- የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት

 

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button
Close
Close