EthiopiaRegions

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ102 ባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰረዘ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ102 ባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰረዘ

አርትስ 09/04/11    

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በእርሻና በዕጣን ሙጫ ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሬት ወስደዉ ባላለሙ 102 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸዉ መሰረዙን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡

ከ164 በላይ ለሚሆኑ ባለሃብቶች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አከባቢ ደንና መሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር ለኢቢሲ እንደተናገሩት በክልሉ ከ6 መቶ በላይ ባለሃብቶች በእርሻ ኢንቨስትመንት፣በዱር ዕጣንና ሙጫ እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ ተሰማርተዉ ይገኛሉ፡፡

የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ ሰሞኑን ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሰረት ከ62 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የኢንቨስትመንት እርሻ መሬት ተቀብለዉ ያላለሙ 102 ባለሃቶች ፈቃዳቸዉ ሙሉ ለሙሉ በመሰረዝ ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲደረግ ተወስኗል ብለዋል የቢሮዉ ሃላፊ አቶ ኢሳቅ፡፡

ፎርጂድ የባንክ ኢንቨስትመንት በማቅረብ ከ1 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ወስደዉ ደን እየጨፈጨፉ ከሰል ሲያመርቱ የተገኙ 3 ባለሃብቶች በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡

ሰፋፊ መሬቶችን ተቀብለዉ በዱር ዕጣንና ሙጫ ዘርፍ የተሰማሩ 20 ባለሃብቶች መካከል የ14ቱ ባለሃብቶች ፈቃድ በመሰረዝ መሬቱን ለአልሚ ባለሃብቶችና ለስራ አጥ ወጣቶች እንዲተላለፍ ዉሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡

ከቀረጥ ነፃ ገብተዉ ለታለመለት ዓላማ ያልዋሉ የ37 ባለሃብቶች ንብረት የሆኑ 56 የእርሻ ትራክተሮችና 26 ፒክአፕ መኪኖችን ባሉበት እንዲታገዱና የገቢዎች ሚኒስቴር ተከታትሎ ህጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድ የኢንቨስትመንት ቦርዱ ወስኗል፡፡

እንዲሁም በአፈፃፀማቸዉ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ሚገኙ 164 ባለሃብቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱም ተገልጿል፡፡

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ከልማት ባንክና ከንግድ ባንኮች ብድር የወሰዱ 113 ባለሃብቶች ብድራቸዉን በአግባቡ እየመለሱ ባለመሆናቸዉ አበዳሪ ተቋማት የህግ አሰራሩን ተከትለዉ እርምጃ መዉሰድ እንዳለባቸዉ ዉሳኔ መተላለፉን አቶ ኢሳቅ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በማዕድን ዘርፍ ለተሰማራ አንድ ባለሃብት ብቻ እስከ 300 ሄክታር የማዕድን መሬት ይሰጥ እንደነበር የተናገሩት ሃላፊዉ በዘርፉ ለተሰማራ ባለሃብት 20 ሄክታር ብቻ እንዲሰጠዉና የተቀረዉን ለመሬት ባንክ ገቢ እንዲያደርግ ዉሳኔ ተላልፏል፡፡

በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ለአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ዉስንነት መስተዋሉን የገመገመዉ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርዱ የተወሰኑ ባለሃብቶችም የፀጥታ ስጋት በመሆናቸዉ እርምጃ ለመዉሰድ መገደዱን አቶ ኢሳቅ ተናግረዋል፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button