Ethiopia

ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የጤና ኤክስቴንሽን ወሳኝ ሚና እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ::

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 26፣ 2013 ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የጤና ኤክስቴንሽን ወሳኝ ሚና እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ:: የግልና አካባቢ ንጽህናን በአግባቡ በመጠበቅ የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቀነስ ለጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም የተሰጠው ትኩረት ውጤት እያመጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የግልና የአካባቢ ንጽህናን ጨምሮ 19ኙ የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን ተግባራዊ ያደረጉ ከ900 የሚበልጡ ግንባር ቀደም ቤተሰቦች ትናንት በባሌ ጎባ ተመርቀዋል።

በግንባር ቀደም ቤተሰቦች ምረቃ ላይ የጎባ ከተማ የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መህፉዛ ጀማል እንደገለጹት በከተማዋ በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካኝነት ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው መርሃ-ግብር የህብረተሰቡ የጤና አጠባበቅና አመለካከት እየተሻሻለ መጥቷል። በዚህም የግልና አካባቢ ንጽህናን ጨምሮ ሌሎች የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን በግላቸው ተግባራዊ የሚያደርጉ ቤተሰቦች እየተበራከቱ መምጣቸውን ገልጸዋል።

ፕሮግራሙን በተሻለ ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ግንባር ቀደም በመሆን ለምረቃ የበቁት ከ900 የሚበልጡ ቤተሰቦች የዚሁ ጥረት አካል ናቸውም ብለዋል፡፡
የጎባ ከተማ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ በበኩላቸው መንግስት በሽታን መከላከል ላይ ያተኮረ ህብረተሰብን ማዕከል ያደረገ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መሰረታዊ ፍልስፍና በሰለጠኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የጤና መልዕክቶችና ተግባራት ወደ እያንዳንዱ ቤትና ቤተሰብ በማድረስ የህብረተሰቡን ንቃተ ጤና በማሳደግ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button