Uncategorized

የውጪ ሃይሎች ከህዳሴው ግድብ እና ከሉአላዊነታችን ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ ጥሪ የሚቀርብበት ሀገር አቀፍ የምሁራን መድረክ ሊካሄድ ነው::

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30፣ 2013  የውጪ ሃይሎች ከህዳሴው ግድብ እና ከሉአላዊነታችን ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ ጥሪ የሚቀርብበት ሀገር አቀፍ የምሁራን መድረክ ሊካሄድ ነው:: የጎንደር ዩንቨርሲቲ ይህን ዓለም አቀፍ ጥሪ የሚቀርብበትን መድረክ በመጪው ሃሙስ ለማካሄድ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ የዩንቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ እንደገለጹት ሀገር አቀፉ የምሁራን መድረክ አላማ የውጪ ሃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ
ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ለማሳወቅ ነው፡፡

በርካታ የውጪ ሃይሎች በአሁኑ ወቅት በህዳሴው ግድብ እና በሌሎች የውስጥ ጉዳዮቻችን ጣልቃ በመግባት መብታችን እና ሉአላዊነታችን እስከ መጋፋት የሚደርሱ ተጽዕኖዎችን እያደረሱ ነው ብለዋል፡፡ መድረኩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ይህን ከዓለም አቀፍ ህጎችና መርሆዎች ያፈነገጠ የውጪ ጣልቃ ገብነት ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ እውነታውን የሚያሳውቁበት አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ስኬት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን በማበርከት የጀመረውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ብሄራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር በማሰብ መድረኩ መዘጋጀቱን ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በመድረኩ በአባይ የዓለም አቀፍ የውሃ ህጎችና የውሃ ችግር አፈታት ዘዴዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሰባት ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ፕሬዘዳንቱ ገልፀዋል፡፡

በሀገሪቱ ከሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች የተጋበዙ ምሁራንን ጨምሮ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የህዳሴው ግድብ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም በክልል ደረጃ የተጋበዙ የውሃ ባለሙያዎች እና ሃላፊዎች በመድረኩ እንደሚሳተፉ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button