Ethiopia

የሠራዊቱን ስም ማጠልሸት በሀገር ላይ አደጋ ለመጣል መሞከር ነው-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014 የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሠራዊቱ ላይ አሉባልታ የሚነዙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠነቀቁ፡፡ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከሌሎች የጸጥታ አከላት ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ላይ ተደቅኖ የነበረውን የህልውና አደጋ በመቀልበስ አኩሪ ገድል መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡


ሠራዊቱ የሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አብራክ ክፋይና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጨረሻው ምሽግ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እሱን መደገፍ የአገርን ህልውና ማጽናት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሠራዊቱን ሥም ባልተገባ መንገድ ማጠልሸትና አሉባልታ መንዛት ግን በአገር ህልውና ላይ አደጋ ለማጣል መሞከር መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡


ኢታማዦር ሹሙ ለመከላከያ ሠራዊት አባላት የተሰጠው የማዕረግ እድገትና ሽልማት በደጀንነት የተሰለፈው ህዝብ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ የተገነባበት ህዝባዊ መሰረትና ያለው ጠንካራ የአመራር ትስስር ላስመዘገበው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው ያነሱት፡፡ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር በመተባበር “ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” ብሎ መነሳቱ በሠራዊቱና ደጀን በሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ቁጭት መፍጠሩንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አብራርተዋል፡፡


የኢትዮጵያን ህልውና ለመጠበቅ በተካሄደው ውጊያ በጀግንነት ጀብዱ ለፈጸሙ የሠራዊቱ አባላት የተበረከተው የማዕረግ እድገት እና ሽልማት በቀጣይ ለአገራቸው ፊት ለፊት የሚቆሙ ጀግኖችን በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም  ነው የተናገሩት፡፡ አሁን ላይ ሠራዊቱ ራሱን ይበልጥ በማደራጀትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አቅሙን በመገንባት የትኛውንም የህልውና አደጋ መቀልበስ በሚያስችል ዝግጁነትና ቁመና ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button