World News

አሜሪካ እና እንግሊዝ በሩሲያ የነዳጅ እና የጋዝ ሽያጭ ላይ እገዳዎችን አሳለፉ


አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2014 21 አሜሪካ እና እንግሊዝ በሩሲያ የነዳጅ እና የጋዝ ሽያጭ ላይ እገዳዎችን አሳለፉ:: ሁለቱ ሀገራት በሩሲያ ላይ የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ጫና የገፉበት ሲሆን ሞስኮ የነዳጅ ምርቷን ለገበያ እንዳታቀርብ ተባብረውባታል፡፡ የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ በሩሲያ የጋዝ ምርት ላይ ያለውን ጥገኝነት በማቆም ለዩክሬን ወረራ ኢኮኖሚያዊ የማዕቀብ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተወሰደው እርምጃ የሩሲያ ኢኮኖሚ ዋና የደም ስር ላይ ያነጣጠረ ነው ብለውታል።


የሃይል አቅርቦት ለሩሲያ ወሳኝ የኤክስፖርት የገቢ ምንጭ ቢሆንም እየተወሰደ ያለው እርምጃ በምዕራባውያን የምርቱ ተጠቃሚዎች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡ የሩሲያ ኢኮኖሚ በኃይል ላይ በእጅጉ ጥገኛ ሲሆን ሀገሪቱ ከሳውዲ አረቢያ እና ከአሜሪካ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ የነዳጅ ዘይት አምራች ነች።


ዋናዎቹ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶች ከሩሲያ መውጣታቸውን የቀጠሉበት ሲሆን ማክዶናልድ እና ኮካ ኮላ ሀገሪቱን ለቀው ከወጡት የቅርብ ጊዜዎቹ መካከል ናቸው። የምዕራባውያኑ እርምጃዎች ከመሰማታቸው በፊት ሩሲያ በአለም ኢኮኖሚ ላይ አሰቃቂ መዘዝ የሚያመጣ ምላሽ እንደምትሰጥ ያስጠነቀቀች ሲሆን ወደ ጀርመን የተዘረጋውን ዋና የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ልትዘጋ እንደምትችል ተናግራለች።

ከማዕቀቡ በኋላ ሩሲያ ወደ ውጭ የምትልካቸውን አንዳንድ ሸቀጦቿን እና ጥሬ እቃዎቿን ለማገድ ማቀዷን ያስታወቀች ሲሆን በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትዕዛዝ ዝርዝር ጉዳዮች አሁንም በጥልቅ እየታዩ ስለመሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በዩክሬን እና ሩሲያ ግጭት ሰበብ ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በአሜሪካ እና እንግሊዝ በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎችም ከዚህ የበለጠ ሊንር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button