Ethiopia

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2014 ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል።
ከቀኑ 10 ሰአት ጀምሮ በአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ‘ካፒቶል ሂል’ ፊት ለፊት በሚካሄደው ሰልፍ ረቂቅ ሕጎቹ የኢትዮጵያን ሕልውና የሚጎዱ በመሆኑ ውድቅ መሆን አለበት የሚሉ መልዕክቶች ይተላለፋሉ ተብሏል፡፡


ሕጎቹ ለረጅም ጊዜ የቆየውን በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚጎዱ እንዲሁም የሁለቱን አገራት ጥቅም የማያስጠብቁ መሆናቸውን የአሜሪካ መንግስት መገንዘብ እንዳለበት የሚያሳስቡ መፈክሮች እንደሚሰሙም ተገልጿል። በሰልፉ ላይ በአሜሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በተጨማሪ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉ ነው የተነገረው፡፡


ሰላማዊ ሰልፉፍ የሚካሄደው የሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕግ ላይ ከሚያደርገው ውይይት አንድ ቀን አስቀድሞ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮችን በማነጋጋርና ማብራሪያ በመስጠት፣ ደብዳቤ በመጻፍ፣ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ በማካሄድ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በቅርቡ በኒው ጀርሲና በካሊፎርኒያ ግዛቶች ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ ረቂቅ ሕጉን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button