loading
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አዲሱ አመት ለመላዉ ኢትዮጵያዉያን የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የሰላም እና የአንድነት እንዲሆን በመመኘት ስብሰባውን አጠናቀቀ

አርትስ 5/13/ 2010
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ በሚካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔና ሀገራዊ ለውጡን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ በመምከር መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከጷጉሜ 2 እስከ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ማጠናቀቁን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በድረ ገፁ ገልፃôል።
ስራ አስፈፃሚው ለሁለት ቀናት ባካሄደው ስብሰባውም ለ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት እና በቀጣይ ሀገራዊ ለውጡን በብቃት ለመምራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክሯል።
ስራ አስፈጻሚው በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በድርጅትና በመንግሰት ስራዎች ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች አፈጻጸምን ሪፖርት በመገምገም የ11ኛው ጉባኤ አቅጣጫዎች ላይም የመከረ ሲሆን፥ የ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ “ሀገራዊ አንድነት፥ ለሁለንተናዊ ብልፅግና’’ በሚል መሪ ቃል የሚያካሂደዉ ግምገማ፣ የሚያስቀምጣቸዉ አቅጣጫዎችና ዉሳኔዎች የሚኖራቸዉ ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አስቀምጧል።
11ኛዉ የኢህአዴግ ጉባኤ የሀገሪቱንና ህዝቦቿን የህልውና አደጋ ላይ የጣሉ ድክመቶችን ለማረም ወሳኝ የለውጥ ሂደት በተጀመረበት ወቅት የሚካሄድ ሲሆን፥ ድርጅቱ ሪፎርም በማድረግ ለመድረኩ ብቃት ያለው የአመራር ቁመና ላይ ማድረስ አስፈላጊ በሆነበት ግዜ ላይ የሚካሄድ ጉባኤ መሆኑ እና ድርጅታዊ ጉባኤው የሁለተኛው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የግማሽ ዘመን አፈጻጸም በመገምገም የቀሪውን ጊዜ የትኩረት አቅጣጫዎች ማስቀመጥ እንደሚጠበቅበት መክሯል።
በዚህም መሰረት በድርጅትና ፖለቲካ፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣በለውጥና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በልማት ስራዎች ላይ የቀጣይ አመታት አቅጣጫዎች ለጉባዔ መነሻ አቅርቧል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታና ለውጡን በብቃት የመምራት አስፈላጊነት በተመለከተ የተጀመረውን ፈጣንና ተከታታይ ለውጥ መሰረት ይዞ እንዲቀጥል ተቋማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ አስይዞ መሄድ እንደሚገባ ከስምምነት ደርሷል።
በዚህም የኢህአዴግን ተራማጅነት፣ አንድነት፣ አንጻራዊ ነጻነት እና አሰራር ምቹነት ለማጠናከር እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የተጀመረውን የመድበለ-ፓርቲ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታውንይበልጥ ለማጠናከር የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት እና የዴሞክራሲ ተቋማትን የማጠናከር፣ የፌደራል ስርዓቱ ብሄረሰባዊና ኢትጵያዊ ማንነት አስማምቶ ለመሄድ የሚያጋጥሙ አመለካከት ችግሮችን መቅረፍ፣ ጠንካራ የመንግስት ቢሮክራሲ ለመፍጠር ሴክተር ተኮር ሪፎርሞች አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቷል።
በተጨማሪም በኢኮኖሚው መስክ እያጋጠሙ ያሉ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝና አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም እየተዳከመ መሄድ፣ የገቢ መሰብሰብ አቅም ዝቅተኛ መሆን እና የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በቀጣይ በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍታት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ስራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር አስተማማኝ ድልድይ ግንባታ የሚያግዙትን የለውጥ መርሆች አንጥሮ ለማውጣት እንዲቻል፣ እሴቶቹና መርሆቹን አባላቱ እንዲያውቋቸውና ለማስረዳት በሚያስችላቸው ቁመና ላይ እንዲገኙ ለማድረግ፤ ሕዝቡም የለውጥ መርሆችን ተገንዝቦ፣ ለለውጡም የሚጠበቅበትን ተሳትፎ በሚያደርግበት የዕውቀትና የተሳትፎ ልክ እንዲገኝ ለማስቻል፤ በቀጣይ እንዲረጋገጥ ለሚታሰበው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አባላትና ሕዝቡ የሚያደርጉት ጠንካራ ትግልና ድጋፍ እንዲቀጥል ለማስቻል የለውጡ መርሆች ላይ ጥልቅ ውይይት አድርጓል።
የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተጀመረው ለውጥ ድርጅቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ የተፈጸመ እንዲሁም ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ መሆኑን በአጽንኦት በመገምገም ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መላው አመራር፣ አባላትና ምልዓተ ህዝቡ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪውን በማቅረብ ስብሰባውን አጠናቋል።
በመጨረሻም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አዲሱ አመት ለመላዉ ኢትዮጵያዉያን የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የሰላም እና የአንድነት እንዲሆን ከልብ እንደሚመኝም ገልጿል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *