loading
አርትስ ዝክረ አድዋ እቴጌ ጣይቱ እቴጌ ጣይቱ ለአድዋ ድል አንፀባራቂ ሚና ተጫውተዋል

አርትስ ዝክረ አድዋ

እቴጌ ጣይቱ

እቴጌ ጣይቱ ለአድዋ ድል አንፀባራቂ ሚና ተጫውተዋል

የእቴጌ ጣይቱ የአድዋ ገድል የሚጀምረው  ለአድዋ ጦርነት መነሻ ከሆነው ከውጫሌ ስምምነት ነው፡፡

ኮንት አንቶኔሊ የውጫሌ ውል እርሱ እንደፈለገው እንደማይሆን እና 17ኛዋ አንቀፅ እንደተሰረዘ በሰማ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ እና አጤ ምኒልክ በተቀመጡበት እልፍኝ ገብቶ  የ 17 ተኛዉ ክፍል ተሰርዞአል ተብሎ ተፃፈ በማለት አጤ ሚኒልክን   ይጠይቃል አጤ ሚኒልክ ም ሁለታችን አንተና እኔ ተነጋግረን አንተ ወደህና ፈቅደህ የተፃፈ ቃል ነዉ ሌላ አልታከለበትም ባስተርጐሚህ የተናገርከዉ ነዉ አሉት። ከዛ ኮንት አንቶኔሊ እንዳልተሳካለት አዉቆ የዉሉን ወረቀት በጫጨቀዉና ጦርነቱ እንደማይቀር ተናግሮ ከልፍኝ እየወጣ እያለ  “እቴጌ ጣይቱ ከት ብለዉ በመሳቅ የዛሬ ሳምንት አድርገዉ በዚህ የሚደነግጥ የለም ሂድ የፎከርክበትን አድርግ እኛም የመጣዉን እናነሳዋለን እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰዉ ከዚህ የሌለ አይምሰልህ የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነዉ እንጅ ሞት አይደለም አሁንም ሂድ አይምሽብህ የፎከርክበትን በፈቀደህ ጊዜ አድርገዉ እኛም ከዚሁ እንቆይሀለን››
“ያንተ ፍላጐት ኢትዮጵያ በሌላ መንግስት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ለማሳወቅ ነው። ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም!! እኔ ራሴ ሴት ነኝ። ጦርነት አልፈልግም። ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” በማለት ፈፅሞ በኢትዮጵያ ሉአላዊነት እንደማይደራደሩ መናገራቸውን  ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መፅሃፍ አስፍረዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ሴቶችን በማስተባበር ትልቅ ስራም ሰርተዋል፡፡ እቴጌ ጣይቱ በአድዋ ዘመቻ ወቅትም የራሳቸውን ጦር እየመሩ ዘምተዋል፡፡

ከጦርነቱ አስቀድሞ ሀገራችን ከ1880 እስከ 1884 ዓ.ም በነበሩት አምስት ዓመታት የከብት በሽታ ገብቶ ከብቶችና ሌሎች እንሳሳት  በማለቃቸው ገበሬው  አርሶ ለማምረት ባለመቻሉ ሀገራችን ከፍተኛ የረሃብ ችግር ውስጥ መሆኗን ጣሊያን የኢትዮጵያ ሰራዊት በረሀብ ምክንያት እንደሚበተን ትልቅ ተስፋን አንግቦ እንደነበርም ጳውሎስ ኞኞ ፅፈዋል፡፡

የመጀመሪያው ስንቅ የማቀበሉ ስራ በአግባቡ እንዲከናወን በማድረግ ሠራዊቱ በረሃብ ምክንያት እንዳይበተን ማድረግ መቻላቸውንም ፓውሎስ ኞኞ በመፅሃፋቸው አስፍረዋል፡፡

ጦርነቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች ይደረግ ስለነበር በአንዱ አቅጣጫ የዘመተው አዝማች ድል አድርጐ እና ምርኮ ይዞ በመመለስ ሲፎክርና ሲያቅራራ ‹‹ድሉ ገና ንጉሡ ሣይመለሱ እዚህ ሆኖ መፎከሩ ምንድነው?›› በማለት እየተቆጡ ሲያበረታቱ እና ሌሎቹን አውደውጊያዎች እንዲያግዙ ሲያደርጉ ነበር፡፡

ጣሊያኖች ወደ መቀሌው ምሽግ በተሸሸጉ ጊዜም  ይህን ሁኔታ የተገነዘቡት እቴጌይቱ የጣሊያኖችን የውኃ ምንጭ በራሳቸዉ ጦር በማስከበብ እና ምንጩን በማሳገድ ውሃ ሲጠማቸው ሽንፈታቸውን እንዲቀበሉ አድርገዋል፡፡ ይህ በመቀሌ የሚገኘው ምንጭም እስከዛሬ ድረስ ውሃ የሚያፈልቅ ሲሆን ለንግስቲቱ መታሰቢያነት ይሆን ዘንድ ‹‹ ማይ እንስቲ›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ትርጓሜውም የሴት ውሃ ማለት ነው፡፡

እቴጌ ጣይቱ የማይተካ ሚና ይኑራቸው እንጂ በጦርነቱ ወቅት በስራቸው ያስተባብሯቸው የነበሩ ወደ 3000 ሴቶችም በጦርነቱ ጉዞ ላይ ሆነ በጦርነት ጊዜ በየቀኑ ሰባትም ስምንትም ምጣድ እየጣዱ እንጀራ ይጋግራሉ ፣ ጠላና ጠጅ ይጠምቃሉ ፣ ወጥ ይሰራሉ ፣ ግብር ያበላሉ ፣ ቁስለኛ ያክማሉ ፣ ውሃ ያጠጣሉ ፣ በፉከራና በእልልታ ተዋጊውን ያበረታቱም ነበር፡፡

በአድዋው ጦርነት የኢትዮጵያ ሴቶች በአዋጊነት ተሳትፈዋል። ጦር መርተው፣ መድፍ አስተኩሰው፣ ወታደር አዘው አዋግተዋል፣ ቀን በውጊያ ማታ ከስንቅ ዝግጅት ሳይነጠሉ ረጅሙን የውጊያ ወራት አሳልፈዋል።

ከብዙው በጥቂቱ እቴጌ ጣይቱ እና ጀግኖች እናቶቻችን ለታላቁ የነፃነት ድል አደዋ ይህን አበርክተዋል፡፡

ክብር ለእቴጌ ጣይቱ እና ለቀደሙ ጀግና እናቶቻችን!

በሰላም ገብሩ ተዘጋጀ

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *