loading
በሀገሪቱ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሸራሸር ፅንፍ የያዙ የፖለቲካ ሀሳቦችን የሚያቀራርቡ መድረኮችን መፍጠር ይገባል አሉ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ

በሀገሪቱ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሸራሸር ፅንፍ የያዙ የፖለቲካ ሀሳቦችን የሚያቀራርቡ መድረኮችን መፍጠር ይገባል አሉ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ

ዶክተር አብይ ይህንን ያሉት በወቅታዊ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነዉ።

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዋናነት የቀረበላቸው ጥያቄ በሀገሪቱ ካለው የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጋር መንግስት እየወሰዳቸው ያላቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው  በሶማሌ ከ30 ሺህ በላይ የታጠቀ ሀይልን ከመቀልበስ ጀምሮ በሀዋሳ በአዲስ አበባ በቡራዮ በወለጋ በሻሸመኔ በጌዲዮና በቤንሻጉል  በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች በፍርድቤት ጉዳያቸዉ እየታየ ነዉ ብለዋል፡፡

ህግን ተከትሎ የህግ የበላይነትን በማስከበሩ ስራ ያሉ ከፍተቶች ቢኖሩም በዚያው አግባብ የሚታዩም ይሆናል ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ለግጭት መንስኤ እየሆነ ነውና ይህን እንዴት ያዩታል የተባሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሬት የባለቤትነት ጉዳይ የህገ መንግስት ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ ህገ መንግስቱ ራሱ የሚዳኘው ነው ብለዋል።

ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በተመለከተም በቁጥጥሩ ሂደት ክፍተት ቢኖረውም ቁጥጥሩን ግን መንግስት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው በምላሻቸው ላይ ያመለከቱት።

የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይም በጋዘጠኞቹ የተነሳው ሌላው ጉዳይ የነበረ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ የማናት የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ከጀርባው ያለውን ጥያቄ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከምንም በላይ ግን ከተማዋን እንዴት እንቀይር፣ ሁሉም ዜጋ ከመጠቀም የሚችልበት ከተማን እንዴት እንፍጠር የሚለው ነው ቀድሞ መነሳት ያለበት ነው ያሉት።

ለኦሮሚያ ክልልም በህገ መንግስቱ የተሰጡ መብቶች ሲባሉ አለአግባብ ከአዲስ አበባ እድገትና መስፋፋት ጋር ከኢንዱሰትሪዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚወጡ በካይ ፍሳሾች የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞንን የሚጎዱ መሆን የለባቸውም እና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎችም ተጠቃሚ መሆን ይገባቸዋል በሚል እንጂ አንድ ኦሮሞ አዲስ አበባ ላይ ከሌሎች በተለየ መልኩ መብት አለው ማለት አይደለም ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል በሚያቀርበው ግብዓት ልክ ይጠቀም የሚል ሀሳብ ነው ሊንፀባረቅ የሚገባው ሲሉም ነው ያስረዱት።

በተጨማሪም በከተማዋ ዙሪያ ያለው ነዋሪ ኑሮም ሊታይ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ 170 ሺህ ቤተሰቦች በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚከናወኑ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መፈናቀላቸውን በማንሳትም እነዚህን ዜጎች መርዳት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የህዝብና ቤተ ቆጠራ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ለመወሰን የሚያስችል እና ስለ ሀገር ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል።

ሆኖም ቆጠራው በመራዘሙ በኩል ባለሙያዎች ያቀረቡት ሀሳብ እንደነበር በማንሳት ያንን መሰረት በማድረግ መራዘሙን አስታውቀዋል።

በግጭት የተፈናቀሉ በርከት ያሉ ዜጎች መኖራቸውንም በማንሳት ወደ ቀያቸው ለመመለስ የየአካባቢዎቹን የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት መሪዎች በማሳተፍ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል ።

ያለፈውን አንድ ዓመት በተመለከተ ሲናገሩም፥ ዓመቱ በርካታ የፖለቲካ ሁነቶች የነበሩበት፣ በርካቶች ተስፋ የሰነቁበት፣ ሌሎች ደግሞ በፖለቲካ ሁኔታው ግራ መጋባት ውስጥ የገቡበት ነበር ብለዋል።

ከዚያ ባለፈ በርከት ያሉ የዲፕሎማሲ ስኬቶች የተገኙበት እንደነበር በማንሳትም ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ ከሌሎች በርካታ ሀገራት ጋር የተከናወነውን የዲፕሎማሲ ስራ በማንሳት ለውጡን ከገንዘብ ጀምሮ በሀሳብና በባለሙያዎች የደገፉበት እንደነበር ገልፀዋል።

በዋናነት ይህንን ለውጥ ማስቀጠል የሚቻለው ግን ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ሲያደርጉ መሆኑን በመግለፅ ይህንንም በመተባበር መንፈስ መፈፀም ይገባል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃንም ይህንን ኃላፊነታቸውን በመወጣት ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ ለማስቀጠል የሚያስችሉ እና ወደ ከፍታ የሚያሸጋገሩ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሸራሸር ፅንፍ የያዙ የፖለቲካ ሀሳቦችን የሚያቀራርቡ መድረኮችን በመፍጠር የሃሳብ ልዩነትን የሚያስታርቅ እድልን ማመቻቸት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *