አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28፣ 2013 በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት ለመመከት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አብን ገለፀ፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚ ተወያይቶ የደረሰባቸውን አቋሞች በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ አብን በመግለጫው የመራጩ ድምፅ እንዲከበር ሰላማዊና ሕጋዊ ጥረት እንደሚያደርግና የሕዝቡን ሐቀኛ ውሳኔ ያለማወላወል እንደሚቀበል አሳውቋል፡፡ በምርጫው የመሳተፉን ውሳኔ ያደረገው በዋነኝነት ከድርጅታዊ ፋይዳዎች ይልቅ ለሀገራዊ ፖለቲካው መረጋጋትና ለዴሞክራሲያዊ ተሞክሮ ግንባታ ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር እንደሆነም ገልጿል፡፡ የምርጫው ሂደት አጠቃላይ ድርጅታዊ ቁመናውን የሚፈትሽበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን እንደሚገነዘብ ነው በመግለጫው ያመላከተው፡፡ በቀጣይም ከሂደቱ ያገኛቸውን ተሞክሮዎችና ትምህርቶች በማካተትና ሁለገብ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ ለብሔራዊ ፖለቲካ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡ የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ቦርቧሪዎች ከተቻለ ኢትዮጵያን ለየዘውጉ አምበሎች በታትኖ ከዓለም ካርታ ለማጥፋት፤ ካልሆነ ደግሞ ውስጣዊ አንድነት የሌላት፣ ደካማና ፍላጎታቸውን ያለማንገራገር የምትቀበል አድርገው ለማሽመድመድ እየተረባረቡ ይገኛሉ ብሏል። በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የብሔራዊ የደኅንነት ስጋት ለመመከት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም አብን ገልጿል፡፡ ማዕከላዊ መንግሥትና በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት ሀገሪቱን ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና በግልጽ ከመወሰን አንስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ ደኅንነት እርምጃ እንዲወስዱም አብን ጥሪ አቅርቧል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሀገር ወዳድ ዜጎችና በተለይም ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ሀገሪቱ ስለገጠማት የብሔራዊ የደኅንነት አደጋ ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት እንዲሰለፉም ጠይቋል፡፡ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን የትግራይ ሕዝብ አስፈላጊውን ጥበቃና እክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡