loading
ለተዝካር ማውጫ የተዘጋጀ 100 ሺህ ብር ለህዳሴ ግድብ የለገሱ ኢትዮጵያዊ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 20፣2013 ኢትዮጵያዊቷ ለወላጅ አባታቸው ተዝካር ማውጫ የተዘጋጀ 100 ሺህ ብር ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ አደረጉ። በጀርመን ሀገር የሚኖሩት ኢትዮጵያዊቷ ወይዘሮ ሌንሳ ተሾመ ለወላጅ አባታቸው ተዝካር ማውጫ የተዘጋጀ 100 ሺህ ብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲውል በማድረጋቸው ከግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። ወይዘሮ ሌንሳ ነሐሴ 17/2013 ዓ.ም የአባታቸው ሰባተኛ ሙት ዓመት ተስካር ለማውጣት ቢዘጋጁም ድግሱን በማስቀረት ለዝግጅቱ የታሰበው የ100 ሺህ ብር ወጪ ለግድብ ግንባታ እንዲውል ገንዘቡን ገቢ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ወይዘሮ ሌንሳ የምስክር ወረቀቱን ከጽሕፈት ቤቱ በተቀበሉበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያዊያን ከተባበሩ በራሳቸው አቅም የትኛውንም ተግባራት ውጤታማ ማድረግ እንደሚችሉ የህዳሴ ግድቡ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ለግድቡ ግንባታ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚያስደስት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ግንባታው ከፍጻሜ እስኪደርስ ድጋፉ ተጠናከሮ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊቷ ያደረጉት ድጋፍ አርዓያነት ያለው ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል። በቀጣይም መሰል ድጋፎች በማድረግ ግድቡን እስከ ፍጻሜው መደገፍ እንደሚገባም ነው ዶክተር አረጋዊ ያሳሰቡት። የጽሕፈት ቤቱ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብረሀም፤ እስካሁን ባለው ጊዜ በተለይ ሕጻናት የልደታቸው ወጪ ለግድቡ ግንባታ እንዲውል መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

ነገር ግን ለሙት ዓመት መታሰቢያ የተዘጋጀ ገንዘብን ለግድቡ ግንባታ በመስጠት በኩል ወይዘሮ ሌንሳ ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከዳያስፖራዉ ማኅበረሰብ 134 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መቻሉ እንደተገለጸ ኢዜአ ዘግቧል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *