loading
በማይካድራ በርካታ የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል-ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 16፣ 2013  የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 30 በማይካድራ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ከ1 ሺህ 600 በላይ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማይካድራው በደረሰው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ላይ ስድስት ወራት የፈጀ ጥናት ሠርቻለሁ ብሏል፡፡ የጥናቱ ዓላማ ድርጊቱን ለዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ ማሳወቅ፣ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡና የተጎዱ ወገኖች እንዲካሱ ማድረግ ነው ተብሏል። በጥናቱ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለዓመታት በወልቃይት ጠገዴና በጠለምት አካባቢ በአማራዎች ላይ የፈጸመው ግፍ ተዳስሷል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኀላፊና መምሕር ባምላክ ይደግ ጅምላ ጭፍጨፋው በ1968 ዓ.ም አሸባሪው ቡድን ያዘጋጀው ፍኖተ መርህ አካል እንደሆነ ገልጸዋል። ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በድምጽ አልባ መሳሪያ ጅምላ ጭፍጨፋ ለሚፈጽሙ ወጣቶችና ለፖሊስ አባላት ስልጠና ተሰጥቷል የወንጀል ድርጊቱን የሚያግዙ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ እንደነበርም በጥናቱ ተረጋግጧል። ከድምጽ አልባ መሳሪያ የሚያመልጡትን በመሳሪያ የሚገድል ቡድን ተዘጋጅቶ እንደነበርም በጥናቱ ተመላክቷል።

በማይካድራ ከተማ የሚኖሩ አማራዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ማሳሰቢያ በመስጠት፣ መታወቂያና ሲም ካርዳቸውን በመሰብሰብም ማንነታቸውን የመለየት ሥራ ተከናውኗል ነው የተባለው፡፡ ለቀናት በቂ ዝግጅት ከተደረገ በኋላም ጥቅም 30 እስከ ለሊቱ 9 ሰዓት ድረስ በአሰቃቂ ሁኔታ ጭፍጨፋው መፈፀሙን ዩኒቨርሲቲው በጥናት ግኝቱ ይፋ አድርጓል፡፡ ሰነዶችን ዋቢ በማድረግ፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች በመጠየቅና የመስክ ምልከታ በማድረግ በተሠራው ጥናት በወልቃይት ጠገዴና በጠለምት አካባቢዎች በርካታ ጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *