በተጭበረበረ መንገድ ለተሸከርካሪው ሊብሬና ታርጋ ሊያወጣ ሲሞክር በቁጥጥር ስር የዋለው ተከሳሽ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ተወሰነበት፡፡
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 በተጭበረበረ መንገድ ለተሸከርካሪው ሊብሬና ታርጋ ሊያወጣ ሲሞክር በቁጥጥር ስር የዋለው ተከሳሽ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ተወሰነበት፡፡ ታደለ ንጉሴ የተባለው ተከሳሽ የሙስናን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ እዲሁም የጉምሩክና የፌደራል
ታክስ አስተዳደር አዋጆችን በመተላለፍ ወንወጀሎች ነው ክስ የተመሰረተበት፡፡ ተከሳሹ በሌላ ግለሰብ ስም በጊዜያዊነት ለቱሪስት አገልግሎት ወደ ሃገር ውስጥ የገባ ተሸከርካሪ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎበት የገባ በማስመሰል ታርጋና ሊብሬ ለማውጣት በራሱ ስም ”አስመጭ“ በሚል በተዘጋጀ ሀሰተኛ ዲክላሪሲዮን ለመገልገል ሲል ነው በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡
የተከሳሽ ድርጅት ማህተም ያረፈበት ሀሰተኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ፣ ተሽከርካሪው የጉምሩክ ፎርማሊቲን አሟልቶ የገባ መሆኑን የሚገልፅ ሀሰተኛ ደብዳቤ በእጁ መገኘቱንም የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡ በዚህም ተከሳሹ በፈፀመው በሀሰት በተዘጋጁ መንግስታዊ ሰነዶች መገልገል፣ ባለስልጣናቱ
የሚጠቀሙበትን ሰነድ ወደ ሀሰት መለወጥና መጠቀም፣ እንዲሁም የተጭበረበሩ ደረሰኞችን መያዝና መጠቀም ወንጀል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ እና ታክስ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል።
ይሁን እንጂ ተከሳሽ ታደለ ንጉሴ ፍርድ ቤት ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ የተጠቀሱትን ወንጀሎች አለመፈፀሙን በመግለጽ ክዶ መከራከሩን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ የሚያስረዱ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ
ድርጊቱን መፈፀሙን በበቂ ሁኔታ በማስረዳቱ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ክሱን በማስረጃ
ደግፎ ማስተባበል አልቻለም።
በዚህም መሰረት ችሎቱ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት ተከሳሽን ያርማል፣ መሰል አጥፊዎችንም ያስተምራል በማለት በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡