loading
በቻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍፃሜ አያክስ አሸንፏል

በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር አንድ ጨዋታ ትናንት ምሽት የተደረገ ሲሆን ዛሬም ሌላኛው ግጥሚያ ይካሄዳል፡፡

በዘንድሮው ውድድር አስገራሚ ጉዞዎችን እያደረገ የሚገኘው የሆላንዱ ክለብ አያክስ አምስተርዳም፤ ከሜዳው ውጭ የእንግሊዙን ቶተንሃም ሆትስፐር 1 ለ 0 በመርታት ወደ ፍፃሜው ለመሻገር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሯል፡፡

በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ የበላይነት የነበራቸው እንግዳዎቹ፤ በቀዳሚው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲያመሩ የነበረ ሲሆን ወጣቱ ዶኒ ቫን ደ ቢክ በ15ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ደግሞ የኔዘርላንድሱን ቡድን በ1 ለ 0 ውጤት ጨዋታውን እንዲያሸንፍ አግዛለች፡፡

ሃሪ ኬንን በጉዳት እና ሶን ሂንግ ሚንን ደግሞ በቅጣት ወደሜዳ ይዘው ሳይገቡ የቀሩት ስፐርሶች በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም ግብ ሳያስቆጥሩ ግን ቀርተዋል፡፡

አያክሶች አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ከመጀመሪያው አጋማሽ የቀዘቀዘ ጊዜን በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ ቢያሳልፉም አስጨናቂ እንቅስቃሴዎችን ግን ከማድረግ አልተቆጠቡም፤ የብራዚላዊው ኔሬስ የግቡን ቋሚ ብረት ለትማ የተመለሰችው ኳስ የምታስቆጭ ነበረች፤ ይህቺ ግብ ብትቆጠር የቡድኑን መሪነት ባሳደገች ነበር፡፡ ኢላማውን በጠበቀ የኳስ ሙከራ የኤሪክ ቴን ሃግ ስብስብ የተሻለ ነበረ፡፡

በሚቀጥለው ሳምንት ዕረቡ የመልሱ ጨዋታ አምስተርዳም ላይ ይደረጋል፡፡ ይህ ጨዋታም ከወዲሁ ይጠበቃል፡፡

ሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይደረጋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *