በኢትዮጵያ አማካይ የመኖሪያ እድሜ 69 ዓመት ደረሰ በኢትዮጵያ 45 የነበረው አማካይ የመኖሪያ እድሜ ምጣኔ ወደ 69 ዓመት ማደጉ ተገለጸ::
አዲስ አበባ፣መጋቢት 5፣2014 በኢትዮጵያ 45 ዓመት የነበረው አማካይ የመኖሪያ እድሜ ምጣኔ ወደ 69 ዓመት ማደጉን በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራ እና ትንተና ማእከል አስታውቋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የጤና አትላስ ይፋ ባደረገበት ወቅት ፤ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1980 አማካይ የመኖሪያ እድሜ ዘመን 45 ዓመት የነበረው በ2019 ወደ 69 ዓመት ማደጉን አስታውቋል። በፈረንጆቹ 1990 ከአንድ መቶ ሺህ ሰዎች የነበረው 2390 የሞት መጠን ወደ 994 ዝቅ ማለቱም ተጠቅሷል።
የጤና አትላሱ በሀገሪቱ የተከሰቱ የጤና ችግሮችን የሚያመላክት ሲሆን መረጃን ለማግኘትና ለመለዋወጥ የሚያስችል በመሆኑ ችግሮችን ይፈታል ሲሉ የብሔራዊ የጤና መረጃ ማደራጃና ማጠናከሪያ ማዕከል አማካሪ ዶ/ር አወቀ ምስጋናው ገልጸዋል፡፡ እስከ መጪው አርብ በሚቆየው ጉባኤ በኢትዮጵያ የጤና መረጃ ስርዓት ትብብር በሚጠናከርበት ሁኔታ ዙሪያ ምክክር ይካሄዳል፡፡