በኢትዮጵያ አየር ሀይል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ የሀሰት መረጃዎች እየወጡ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ፡፡
አዲስ አበባ፣ ህዳር 08፣ 2013 በኢትዮጵያ አየር ሀይል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ የሀሰት መረጃዎች እየወጡ መሆኑን
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ፡፡ እንደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ በሁለት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት፣ በመቀሌ
የአየር ጥቃት መደረጉን የሚገልጹ አርዕስት እና አጭር ቪዲዮዎች ወጥቷል፤ እነዚህ መረጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይሉ ሳያረጋግጡ በትህነግ መረጃ ላይ ብቻ የተመሠረቱ ሐሰተኞች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ሠላማዊ ሰዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው ተደርጎ የተገለጸው ሐሰት መሆኑም ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ በወሳኝ የትህነግ ዒላማዎች ላይ ከመቀሌ ከተማ ውጭ የታለመ የአየር ጥቃት ማካሄዱን ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ያስታወቀው፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ዒላማን በጥንቃቄ መምታትን መሠረት ያደረገ እንደሆነም ገልጿል። ትህነግ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃቱን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ በሠላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ሲል ከከተሞች የራቀ ጥቃት ላይ እንዳተኮረም ነው ያስታወቀው፡፡