loading
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በደረጃ ሰንጠራዡ አናት ላይ የሚገኙት ክለቦች አሸንፈዋል

የሊጉ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት ሁለት ግጥሚያዎች ሲከናወኑ፤ መከላካያ በፋሲል ከነማ ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር የ4 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ለአፄዎቹ ኢዙ አዙካ ሁለት፣ ኤፍሬም ዓለሙ እና የመከላከያው ዓለምነህ ግርማ በራሱ መረብ ላይ የአሸናፊነት ጎሎችን አስቆጥረዋል፡፡ ፋሲል በሲዳማ ተነጥቆ የነበረውን የሁለተኛ ደረጃ መልሶ ተረክቧል፡፡

መቖለ 70 እንደርታ ትግራይ ላይ አዳማ ከተማን በአማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ያሬድ ከበደ ግቦች 2 ለ 1 ረትቶ የሊጉን መሪነት አጠናክሯል፤ አዲስ ህንፃ የእንግዳውን ቡድን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡
በትናንትናው ዕለት ሊካሄድ የነበረው የሀዋሳ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ፤ ሀዋሳ ከተማ ላይ ባለው የፀጥታ ዋስትና ዕጦት ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡
ቅዳሜ ዕለት በጉጉት በተጠበቀው የኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከነማ ግጥሚያ፤ ቡናማዎቹ ባልተገመተ የ5 ለ 0 ውጤት ድል አድርገዋል፡፡ አቡበከር ናስር እና ሁሴን ሻባኒ እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ቀሪዋን እያሱ ታምሩ ከመረብ አገናኝቷል፡፡
በሌሎች የእለቱ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከነማ ሜዳው ላይ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 ሲረታ፤ ደደቢት በጅማ አባ ጅፋር የ 1 ለ 0 ሽንፈት ገጥሞታል፡፡
በደቡብ ፖሊስ እና ወላይታ ድቻ መካከል ሊደረግ የነበረው ግጥሚያ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡
ዓርብ ዕለት ሲዳማ ቡና ሀዋሳ ላይ ስሑል ሽረን 3 ለ 2 መርታቱ ይታወሳል፡፡
መቐለ ሊጉን በ45 ነጥብ ይመራል፣ ፋሲል በ37 ይከተለዋል፣ ሲዳማ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ አንሶ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ጅማ አባ ጅፋር በ34 አራተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
መከላከያ፤ ስሑል ሽረ እና ደደቢት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ናቸው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *