loading
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን የሚያጠናክሩበትን ዕድል አልተጠቀሙበትም

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን የሚያጠናክሩበትን ዕድል አልተጠቀሙበትም

በሊጉ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተካዱ ጨዋታች በአዲስ አበባ እና ክልል ስታዲየሞች ላይ እየተካሄዱ ነው፤ ትናንት 3 ግጥሚያዎች ሲከናወኑ፤ አዳማ ከተማ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡

ይህን ተከትሎ ፈረሰኞቹ የሊጉን መሪነት ከተከታዮቻቸው ለማስፋት የነበራቸውን ዕድል አልተጠቀሙበትም፡፡ ቢሆንም ግን በ26 ነጥብ እና 13 ንፁህ ግቦች የሊጉ መሪነት በእጃቸው እንዳለ ነው፡፡

ትግራይ ስታዲየም ላይ ደደቢትን የገጠመው መከላከያ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ድል አድርጓል፡፡ አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ሁለት እንዲሁም ፍሬው ሰለሞን ያስቆጠሯቸው ግቦች፤ የጦሩ ቡድን ከቀናት በፊት በመቐለ 70 እንደርታ የደረሰበትን አስደንጋጭ ሽንፈት በደደቢት ላይ እንዲያካክስ አግዞታል፡፡

ምንይሉም የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት አሁንም በ11 ጎሎች አጠናክሮ መምራቱን ቀጥሏል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ ሁለቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክለቦች ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ባገናኘው ግጥሚያ፤ በሲዳማ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ ይህን ተከትሎ ሲዳማዎች ነጥባቸውን እኩል ከጊዮርጊስ ጋር በማስተካከል በግብ ክፍያ አንሰው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተሰይመዋል፡፡

የተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ፤ መቐለ 70 እንደርታ በትግራይ ስታዲየም የጎንደሩን ፋሲል ከነማ ያስተናግዳል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው ወቅታዊ አቋም የተነሳ ብርቱ ፉክክር ይደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን መቐለ የሚረታ ከሆነ ነጥቡን ወደ 26 ከፍ በማድረግ ደረጃውን የሚያሻሽል ይሆናል፤ በአንፃሩ ድል ወደ አፄዎቹ የምታዘነብል ከሆነ ደግሞ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ከፍ የሚል ይሆናል፡፡

ሌላኛው ጨዋታ በባህር ዳር ከነማ እና ስሑል ሽረ መካከል በባህር ዳር ግዙፍ ስታዲየም ሲካሄድ ጅማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር ድሬዳዋ ከነማን ያስተናግዳል፡፡

ሁሉም ግጥሚያዎች በተመሳሳይ ቀን 9፡00 ይካሄዳሉ ተብሏል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *