በእንግሊዝና ፈረንሳይ መካከል ተጥሎ የነበረው የጉዞ እገዳ መነሳቱን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ዳግም ተጀምሯል፡፡
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 14፣ 2013 በእንግሊዝና ፈረንሳይ መካከል ተጥሎ የነበረው የጉዞ እገዳ መነሳቱን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ዳግም ተጀምሯል፡፡ በእንግሊዝ አዲሱ የኮሮናቫይረስ በመከሰቱ በርካታ ሀገራት የጉዞ እቀባ መጣላቸውን የሚታወስ ሲሆን ፈረንሳይም አንዷ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አሁን ላይ ሀገራቱ በደረሱት ስምምነት መሰረት በእንግሊዝና ፈረንሳይ መካከል የሚደረጉ የባቡር ፣የአየርና የባህር ጉዞዎች ዳግም እንደሚጀመሩ ነው የተነገረው፡፡
የፈረንሳይ ዜጎችና በፈረንሳይ የሚኖሩ የእንግሊዝ ዜጎች በቅርቡ ተመርምረው ከኮቪድ 19 ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ በመያዝ መጓጓዝ ይችላሉ ተብሏል፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ሳቢያ ድንበሮች መዘጋታቸውን ተከትሎ በርካታ ተሸከርካሪዎች መንጎችን አጨናንቀው ታይተዋል፡፡
ፈረንሳይና እንግሊዝ እገዳውን ለማንሳት ከስምምነት ላይ ቢደርሱም ጣሊያን ፣ ህንድና ፓኪስታንን ጨምሮ ከ50 በላይ ሀገራት አሁንም እቀባዎችን መጣላቸውን ቀጥለዋል፡፡