በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማንችስተር ሲቲ አሸንፏል
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማንችስተር ሲቲ አሸንፏል
የ22ኛ ሳምንት መርሀግብር የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ትናንት ምሽት ኢቲሃድ ላይ በማንችስተር ሲቲ እና ወልቨርሃምፕተን ወንደረርስ መካከል ተካሂዷል፤ ወልቭስ ታላላቅ ክለቦችን ሲገጥም የሚያሳየውን ፉክክር ተከትሎ የምሽቱን ጨዋታ ተጠባቂ አድርጎት ነበር፡፡
በምሽቱ በተደረገው ግጥሚያ የፔፕ ጓርዲዮላው ሲቲ የ3 ለ 0 ድል በወልቭስ ላይ ተቀዳጅቷል፡፡
ድሉን ተከትሎ ከሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ከሰባት ወደ አራት ሲያጠብ ከተከታዩ ቶተንሃም ደግሞ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት አስፍቷል፡፡
ለሲቲ ብራዚላዊው ጋብሪየል ጀሱስ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር፤ ተቀይሮ የገባው ኬቨን ዲ ብሯይኔ ያሻገራትን ኳስ ደግሞ ኮነር ኳአዲ በራሱ መረብ ላይ ማሳረጊያዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
የወልቭሱ ዊሊ ቦሊ በ19ኛው ደቂቃ ቤርናርዶ ሲልቫ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት ቀጥታ ቀይ ካርድ ተመልክቷል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ፔፕ ጓርዲዮላ ‹‹በ10 ተጫዋች ሆነው በጥልቅ ሲከላከሉ ነበር ፤ ቀላል አልነበረም፤ ኳሷን ወደ ሳጥን ውስጥ ለመጣል ታታሪ መሆን ይጠበቅብን ነበር›› ብለዋል፡፡
የወልቭሱ አሰልጣኝ ኑኖ እስፒሪቶ ሳንቶ ደግሞ ‹‹ቀይ ካርዱ ብቻ ጨዋታውን አልቀየረውም፤ ነገር ግን ግብ የተቆጠረብን መንገድ ከረዥም ርቀት በሚሻሙ ኳሶች ነበር፤ ቀይ ካርዱ ደግሞ ሁሉን ነገር አስቸጋሪ አድርጎብናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ሊጉን ሊቨርፑል በ57 ነጥብ ይመራል፤ ማንችስተር ሲቲ ደግሞ በ53 ሁለተኛ፣ ቶተንሃም በ48 ሶስተኛ እንዲሁም ቼልሲ በ47 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡