loading
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ ሲሸነፍ ዩናይትድ ከተከታታይ ድል በኋላ ነጥብ ጥሏል፡፡

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ ሲሸነፍ ዩናይትድ ከተከታታይ ድል በኋላ ነጥብ ጥሏል፡፡

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሀግብር ትናንት ምሽት ስድስት ያህል ግጥሚያዎች ተካሂደዋል፡፡

በሁሉም ጨዋታዎች የዌልሱን ክለብ ካርዲፍ ከፈረንሳዩ ኖንት በ15 ሚሊየን ፓውንድ ዋጋ ተቀላቅሎ፤ ወደ አዲሱ ክለቡ ሲበር ደብዛው የጠፋውን አርጀንቲናዊ ኢሚሊያኖ ሳላ ታስቦ አምሽቷል፡፡

በምሽቱ ፍልሚያዎች አርሰናል ኢምሬትስ ላይ ካርዲፍን አስተናግዶ የ2 ለ 1 ድል አስመዝግቧል፡፡

የካርዲፉ ብሩኖ ኢኮኤል ማንጋ በሲያድ ኮላሲናች ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ፔር ኤምሪክ ኦባማያንግ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ አደረገ፤ ፈረንሳያዊው አጥቂ አሌክሳንደር ላካዜት ደግሞ ተጨማሪ ጎል አክሎ የመድፈኞቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡

ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ሜንዴዝ ላይንግ በጭማሪ ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ቡድኑን በባዶ ከመሸነፍ አድናለች፡፡

ወደ ሴንት ጀምስ ፓርክ አቅንቶ በራፋኤል ቤኒቲዝ የሚመራውን ኒውካስትል ዩናይትድ የገጠመው ማችስተር ሲቲ ደግሞ የ2 ለ 1 ሽንፈት ተጎንጭቶ ተመልሷል፡፡

ማንችስተር ከተማ ላይ በኦልትራፎርድ በርንሊን ያስተናገዱት ዩናይትዶች ከኋላ ተነስተው ባስቆጠሯቸው ጎሎች ታግዘው ከሽንፈት አምልጠዋል፡፡

በሲን ዳይች የሚመራው በርንሊ በአሽሊ ባርንስ እና ክሪስ ውድ ሁለት ግቦች 2 ለ 0 ሲመራ ቢቆይም፤ ቀያይ ሰይጣኖቹ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ፖግባ በፍፁም ቅጣት እና ቪክቶር ሊንደሎፍ በጨዋታ ያከላት ግብ ሜዳቸው ላይ አንድ ነጥብ እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡

በምሽቱ ሌሎች ግጥሚያዎች ኢቨርተን ከሜዳው ውጭ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘውን ሀደርስፊልድ 1 ለ 0 ድል አድርጓል፡፡ የክላውዲ ራኔሪው ፉልሃም ከ2 ለ 0 መመራት ተነስቶ ብይተንን በ4 ለ 2 ውጤት አሸንፏል ፡፡ ወልቭስ ዌስት ሃምን 3 ለ 0 ረትቷል፡፡

የሊጉ አራት ፍልሚያዎች ዛሬ ምሽት የሚቀጥሉ ሲሆን 4፡45 ሲል የማውሪዚዮ ሳሪውን ቼልሲ ወደ ዲንኮርት አቅንቶ በርንማውዝን ይጎበኛል፤ የለንደኑ ክሪስታል ፓላስ ደግሞ ወደ ደቡብ ጠረፍ አምርቶ ሴንት ሜሪ ላይ ሳውዛምፕተንን ይፈትናል፡፡

ምሽት 5፡00 ሲል ሊቨርፑል በአንፊልድ ሮድ ሌስተር ሲቲን ያስተናግዳል፡፡ የማውሪሲዮ ፖቼቲኖው ቶተንሃም ዊምብሌ ላይ ከሽንፈት ለመውጣት እያለመ ዋትፎርድን በተመሳሳይ ሰዓት ይገጥማል፡፡

ሊጉን ሊቨርፑል በ60 ነጥብ ይመራል ፤ ማ.ሲቲ በ56 ሁለተኛ፤ ቶተንሀም በ51 ሶስተኛ፤ ቼልሲና አርሰናል በተመሳሳይ 47 ነጥብ አራተኛና አምስተኛ እንዲሁም ማ.ዩናይትድ በ45 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *