በካርቱም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ አልደገፉም የተባሉ አንድ የሃይማኖት አባት ከመስጊድ ተባረሩ
በካርቱም አንድ የሀይማኖት አባት በሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ባለመደገፋቸው ህዝቡ ከመስጊድ አባርሯቸዋል ተባለ ።
ሱዳን ውስጥ ካሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀይማኖታዊ መሪዎች አንዱ የሆኑት ኢማም አብዱል ሀይ ዩሱፍ ተቃውሟውን እየመሩ አይደለም በሚል ከአማኞች በቀረበባቸው ውንጀላ ነው ከመስጊድ የተባረሩት።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምስል፤ መንግሥትን በመደገፍ የሚታወቁትን እኚህን ኢማም አንድ ግለሰብ ሲቆጣቸው ታይቷል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ባለፈው አርብ ዕለት ከስግደት በኋላ የአልበሽር አገዛዝ መውደቅ አለበት የሚል ተቃውሞ ተነስቶ አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመው ፖሊሶች ሰልፉን በትነውታል።
የሱዳን ተቃውሞ የተቀጣጠለው መንግሥት በነዳጅና በዳቦ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉን ካስታወቀ በኋላ ሲሆን ባለፉት ሦስት ሳምንታት 22 ሰዎች መገደላቸውም የሚታወስ ነው።