loading
በዋግኽምራ ዞን 150 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተመረቀ፡፡

አዲስ አበባ፣የካቲት 8፣ 2013 በዋግኽምራ ዞን 150 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተመረቀ፡፡ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ድሃና ወረዳ 150 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተመርቋል። በምርቃቱ ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰም ማሞና የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮን ጨምሮ የክልልና የብሔረሰብ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ፕሮጀክቱ ከ34 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ተመላክቷል። በዚህም የባርግባ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በድሃና ወረዳ አምደወርቅ ከተማን ጨምሮ ጭላ፣ ጋኪው፣ ብርብራ እና ሽማምዳ የተሰኙ የገጠር ከተሞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ከዋን ወሽ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በ120 ሚሊየን ብር መነሻ የተጀመረው ፕሮጀክት ተጨማሪ የትራንስፎርመር እና ሌሎች ወጪዎች ተጨምረውበት እስከ 150 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ከድሃና ወረዳ ዋና ከተማ አምደወርቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባርግባ ወንዝን በመሳብ የተሠራ መሆኑን አብመድ ዘግቧል፡፡ ከዚህ ቀደም በዋግህምራ ያለዉን ንጹህ መተጥ ዉሃ እጥርት አርትስ ቴሎቭዥን በቦታዉ ተገኝቶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *