በደቡባዊ ምስራቅ የህንድ ግዛቶች የተከሰተው አውሎ ንፋስ በርካታ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ ጥሏል::
አዲስ አበባ፣ ህዳር 16፣ 2013 በደቡባዊ ምስራቅ የህንድ ግዛቶች የተከሰተው አውሎ ንፋስ በርካታ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ ጥሏል:: ሳይክሎን ኒቫር በመባል የሚታወቀው አውሎ ንፋስ በደቡብ ምስራቅ ህንድ በሚገኙ ሶስት ግዛቶች በፍጥነት እየገሰገሰ መሆኑን ተከትሎ ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡
ሰዎች በአደባባይ እንዳይሰባሰቡና ተጨማሪ መመሪያዎች እስኪተላለፉላቸው ድረስ በጥንቃቄ እንዲቆዩ የአካባቢው ባለስልጣናት አስጠንቅቀዋል ነው የተባለው፡፡ አደጋው ሊያደርስ የሚችልውን ጉዳት መከላከል ሲባልም መንግስት ከ1 ሺህ በላይ የነፍስ አድን ሰራተኞችን በስፍራው አሰማርቷል፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው አየአውሎ ንፋስ አደጋው የተጋረጠባቸው ታሚልናዱ፣ ፓዱቸሪና አንድራ የተባሉ የህንድ ግዛቶች ናቸው፡፡ የሀገሪቱ የአየር ትንበያ ተቋም አውሎ ንፋሱ በነዚህ ግዛቶች በቀጣዮቹ ቀናት ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ትንበያውን ተናግሯል፡፡ በትንበያው መሰረት አውሎ ንፋሱ ከባድ ዝናብ እንደሚያስከትልና በሰዓት እስከ 145 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ሊኖረው ስለሚችል አደገኝነቱ እንደሚያይል ይጠበቃል፡፡ ህንድ በቅርቡ በከባድ አውሎ ንፋስ ተመትታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውና በርካታ ንብረት መውደሙ የሚታወስ ነው፡፡