loading
በጋምቤላ ክልል 36 የእርሻ ፕሮጀክቶች ጠፉ፡፡

በጋምቤላ ክልል 36 የእርሻ ፕሮጀክቶች ጠፉ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋምቤላ ክልል 36 የእርሻ ፕሮጀክቶች መጥፋታቸውን  ገልጸ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ፕሮጀክቶች ተሰማርተው የሚገኙ ባለሃብቶች ያሉበትን ሁኔታ ለመመልከት በጋምቤላ ወረዳ በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርጎ ነበር::

የቡድኑ አባላት ብድርና መሬት ወስደው ስራ ያልሰሩ፣ ብድር ሳይወስዱ ስራ የሰሩ ፕሮጀክቶችን መመልከቱን ገልጿል፡፡

ይህንን ተከትሎም ቡድኑ በጋምቤላ ወረዳ የሚገኙ 6 ሳይቶችን የተመለከተ ሲሆን፥ ከስድስቱ መካከል ሁለቱ በትክክል ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ታዝቧል።

ቀሪዎቹ ግን ስራቸውን በትክክል እንዳልሰሩ ኮሚቴው የታዘበ ሲሆን፥ አንድ ባለሃብት በራሱ ስም፣ በባለቤቱና በልጁ ስም 1 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ወስዶ ወደ ስራ እንዳልገባ አረጋግጧል።

ባለሃብቶች መሬቱን ከተረከቡ በኋላ የምንጣሮ ስራ ሰርተው ጥለው እየጠፉ እንደሆነና መሬቱ ለታለመለት አላማ አለመዋሉን ተመልከቷል።

ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ ትልልቅ ዛፎች ያለ አግባብ መመንጠራቸው በአካባቢው ማህበረሰብም ቅሬታ እንደፈጠረ የተገለፀ ሲሆን፥ በክልሉ ላይ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ እያስከተለ እንደሚገኝም የክልሉ አመራሮች ተናግረዋል።

ቡድኑ ባደረገው ምልከታ በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች 20 ሲሆኑ፥ ያለባቸው ብድር 323 ሚሊየን 832 ሺህ 195 ብር ነው።

የተለያዩ ድክመቶች ያሉባቸው ፕሮጀክቶች 133 ሲሆኑ፥ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር
ብድር እንዳለባቸው ቡድኑ በምልከታው አረጋግጧል።

እንዲሁም እርሻቸውን ጥለው የጠፉ ፕሮጀክቶች ብዛት 36 ሲሆኑ፥ 654 ሚሊየን 320 ሺህ 044 ብር እንደተበደሩ ቡድኑ ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የብድር ሁኔታ ትንተና መሰረት ብዛታቸው 117 የሆኑ ፕሮጀክቶች የብድር አመላለስ ሁኔታቸው አጠራጣሪ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ የያዙትም የብድር ገንዘብ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንደሆነ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል 44 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች በኪሳራ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ የያዙትየብድር ገንዘብ ብዛት 902 ሚሊየን 779 ሺህ 464 ብር መሆኑ ተነግሯል።

ምንጭ ፤- የተወካዮች ምክርቤት

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *