ባለፉት 24 ዓመታት በኢትዮጵያ በትምህርትና ስልጠና ሥርዓት በታዩ ችግሮች ዙርያ ዛሬ ውይይት ይደረጋል
የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ከዛሬ ጀምሮ የሚደረገው የውይይት መድረክ ዋነኛ ዓላማ ለፍኖተ-ካርታው ዝግጅት እንዲረዳ በተዘጋጀው የመጀመሪያ ደረጃ ረቂቅ ጥናት ዙሪያ ውይይት በማድረግ ለፍኖተ-ካርታው ዝግጅት የሚረዳ ተጨማሪ ግብዓት ለማሰባሰብ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የማሻሻያ ሀሳቦች ዙሪያ በሚደረገው ውይይት በተሳታፊዎች የሚቀርቡ ተጨማሪ የማሻሻያ ሀሳቦች በቂ ውይይት ከተደረገባቸውና መግባባት ከተደረሰባቸው በኋላ ለ15 ዓመታት ተግባራዊ እንዲሆን በዝግጅት ላይ ለሚገኘው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ግብዓት በመሆን ጥቅም ላይ እንደሚውል ተነግሯል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በድረ ገጹ እንዳስታወቀዉ በጥናቱ የተለዩ የትምህርትና ስልጠና ችግሮችን በመፍታት ከ17ቱ ዘላቂ የልማት ግቦች መካከከል በ4ኛ ደረጃ የተቀመጠውን የትምህርት ልማት ግብ እንደ ሀገር ለማሳካትና አገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በዉይይቱም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሙሁራን ፣ ተመራማሪዎች ፣የመምህራን ማህበር፣ ሲቪክ ማህበራት እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሰታፊ ይሆናሉ፡፡