ባለፉት 9 ወራት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ከተጓጓዙ ከ29 ሚሊየን በላይ መንገደኞች 87 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ተገኝቷል- የትራንስፖርት ሚኒስቴር
ባለፉት 9 ወራት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ከተጓጓዙ ከ29 ሚሊየን በላይ መንገደኞች 87 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር መገኘቱን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የክፍያ ጉዳናዎችን በተመለከተም የክፍያ መንገድ ኢንተርፕራይዝ ባለፉት 9 ወራት 6 ሚሊየን 38 ሺህ 800 ተሽከርካሪዎችን ምልልስ በማስተናገድ ከ191 ነጥብ 4 ሚለየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተነግሯል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር የ9 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ለተጠቃሚዎች ፈጣን አገለግሎት እንዲሰጥ እና ለጉዞም አመቺ እንዲሆን በማሰብ ባቡሮቹ በየጣቢያዎቹ የሚደርሱበትን የጊዜ ረዝማኔ ለመቀነስ ተሞክሯል።
በዚህም መሰረት ከምስራቅ ወደ ምእራብ የሚጓዘውን የባቡር ጉዞ ከ15 ደቂቃ ወደ 12 ደቂቃ ዝግ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፥ ከሰሜን ወደደቡብ የሚጓዘውን የባቡር መስመር ደግሞ ከ20 ደቂቃ ወደ 15 ደቂቃ ዝቅ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።
እንደሚኒስቴሩ ሪፖርት ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት 9 ወራት በተሰራው ስራ የሀገር አቋራጭ አውቶብስ ሰምሪት መስመርን ቁጥር ወደ 223 ከፍ ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው።
የመደበኛና ወቅታዊ ከባድ የመንገድ ጥገና ስራዎችን በተመለከተም በ9 ወራት ውስጥ ከ13 ሺህ 228 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጥገና ስራዎች መከናወናቸው ነው በሚኒስቴሩ ሪፖርት ላይ የተመለከተው ።
በሀገሪቱ የነበረው የፀጥታ ችግር እና የተቋሙ የኮንትራት አስተዳደር አቅም ውስንነት ባለፉት 9 ወራት ላከናወናቸው የመንገድ ጥገና ስራዎች ስኬት እንቅፋት እንደሆኑበት ሚኒስቴሩ በሪፖርቱ አመልክቷል።