ብላቴናው አፍጋናዊ ሜሲ በታሊባን ዛቻ ከመኖሪያው ቀየው ተሰደደ
ብላቴናው አፍጋናዊ ሜሲ በታሊባን ዛቻ ከመኖሪያው ቀየው ተሰደደ
አርትስ ስፖርት 28/03/2011
የሰባት አመቱ ትንሹ አፍጋኒስታዊ ሜሲ ሙርታዛ አህማዲ፤ በ2016 የሜሲ ስምና 10 ቁጥር ያረፈበት ሰማያዊና ነጭ የአርጀንቲና የፕላስቲክ ማሊያ ለብሶ ፎቶ ተነሰቶ ድረ ገፆች ላይ ከተለጠፈ በኋላ ዝነኛ ሁኗል፤ ብላቴናውና ቤተሰቡ ከዚያ ክስተት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ከመኖሪያው እንዲሰደድ ተገድዷል፡፡
ፎቶው በኦንላይን ሰፊ ሸፋን ካገኘ በኋላ በኳታር ዶሃ በነበረ የባርሴሎና የወዳጅነት ጨዋታ ሙርታዛ ከሜሲ ጋር ተገናኝተው፤ ወደ ሜዳ ይዞት ገብቶ ሜዳ ላይ ሲቦርቅ ተመልክተነዋል፡፡
የሙርታዛ ቤተሰብ እንዳሉት ከታሊባን ዛቻ ስለደረሳቸው ከአፍጋኒስታን መኖሪያቸው እንደተሰደዱ አስታውቀዋል፡፡ ቤተሰቡ ታጣቂዎች ኢላማ ባደረጓት የደቡብ ምስራቅ ጋዝኒ ግዛት የሚኖሩ ሲሆን አሁን ወደ ዋና ከተማዋ ካቡል አቅንተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በ2016 የአጭር ጊዜ የስደት ቆይታ በፓኪስታን ያደረጉ ሲሆን በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ለኤ ኤፍ ፒ ተናግረዋል፡፡
እንደ ቤተሰቡ ገለፃ ከሆነ ሙርታዛ ዝነኛ መሆኑ በታሊባን ኢላማ ውስጥ መውደቃቸውንና እንድ የአካባቢው አፄ በጉልበቱ የሆነ ሰው አሁን ሀብታም ናችሁ፤ ከሜሲ የተሰጣችሁን ገንዘብ ልትሰጡ ይገባል አሊያ ልጃችሁን እንነጥቃችኋለን እንደተባሉ አናት ሻፊቃ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልፀዋል፡፡ አናትም በእኩለ ሌሊት በቤታቸው ላይ የተኩስ ድምፅ ከተከፈተ በኋላ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ቤታቸውን ጥለው ተሰድደዋል፡፡
ካቡል ላይ ሁኖ ሙርታዛም ሜሲን ናፍቄዋለሁ ይላል፣ አንድ ቀንም በድጋሜ እንደሚገናኘው ተስፋ ያደርጋል፡፡ ሜሲን ሳገኘው ሰላም እንዴት ነህ እለዋለሁ፤ ከዚያም እሱም አመሰግናለሁ ሙርታዛ ደህንነትህ ይብዛ ይለኛል፤ ከእርሱ ጋር ወደ መጫወቻ ሜዳ በመሄድ ሲጫወትም እመለከተዋለሁ ብሏል ብላቴናው፡፡
የሙርታዛ ቤተሰብ ሽያዎች የሚበዙበት የሀዛራ አናሳ ጎሳ አካል ሲሆኑ በሱኒ ታሊባኖች ኢላማ ውስጥ ናቸው፡፡