ተመራቂ ሴት ተማሪዎችን ከቀጣሪዎች እና ከስኬታማ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ጋር የሚያገናኝ አዲስ ፕሮግራም ሊጀመር ነው
ተመራቂ ሴት ተማሪዎችን ከቀጣሪዎች እና ከስኬታማ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ጋር የሚያገናኝ አዲስ ፕሮግራም ሊጀመር ነው
ፕሮግራሙ ለሶስት አመታት የሚቆይ ነው ተብሏል
ኤዩሪያን ሶሊውሽን የተባለ ተቋም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት መሪ የተባለ የአመራር እና ማማከር አገልግሎት በነገው ዕለት ይፋ ያደርጋል።
ይህ ፕሮግራም በየዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የመጨረሻ አመት ተመራቂ ተማሪዎች ከቀጣሪ ተቋማት እና ከሴት ስራ ፈጣሪ ባለሃብቶች ጋር የሚገናኙበትን መንገድ የሚያመቻች ነው ተብሏል።
ኤዩሪያን ሶሊውሽን ለአርትስ ቴሌቪዠን በላከው መግለጫ እንዳብራራው ይህ ፕሮግራም ወጣት ሴቶች የአመራር እውቀታቸው እንዲሰፋ እና የግንኙነት መረባቸው እንዲጠናከር በማድረግ ራሳቸውን የሚገልጡበት እና ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበትን መንገድ ይከፍታል ብሏል።
ልምድ እና መረጃ ልውውጥ እውቀትና ክህሎት ኖሯቸው ነገር ግን ተደብቀው ራሳቸውን ማውጣት ያልቻሉ ሴት ወጣቶች በእውቀታቸው የሚያገለግሉበት እና በችሎታቸው የሚጠቀሙበትን እድል ያሰፋል የሚለው ድርጅቱ ፕሮግራሙ ለሚቀጥሉት ሶስት አመታት እንደሚቆይ ጠቁሟል።
የመጀመሪያው የማማከር ፕሮግራም ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት የሚካሄድ ሲሆን ሰልጣኞች በአመራር ክህሎት የሚሰጣቸው ስልጠና እና የማማከር አገልግሎት በጎ ፍቃደኛ በሆኑና በተመረጡ አሰልጣኞች ይካሄዳል ነው የተባለው።