ቻይና እና ጀርመን በኮቪድ-19 ክትባት ስርጭት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያችል ውይይት አደረጉ::
አዲስ አበባ፣ ህዳር 16፣ 2013 ቻይና እና ጀርመን በኮቪድ-19 ክትባት ስርጭት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያችል ውይይት አደረጉ:: የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ከቡድን 20 ጉባኤ በኋላ ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት አውሮፓ በሁለተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስለመጠቃቷና ችግሩን እንዴት በጋራ መፍታት እንደሚቻል ተነጋግረዋል፡፡
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂምፒንግ ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ቻይና ከጀርመን ጋር ለመስራት ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ትብብር በተለይ አስተማማኝ እና በቂ አቅርቦት ያለው ክትባት መኖሩን ማረጋገጥና ለድሃ ሀገራት እንዴት ተደራሽ ማድረግ ይቻላል በሚለው ሀሳብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው ትብብር በአውሮፓና ቻይና መካከል የሚደረግ ሁለንተናዊ ግንኙነት ነው ያሉት ሜርክል ከኮሮናቫይረስ ወጭ በኢንቨስትመንት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሌሎችም ዘርፎች ከቻይና ጋር አብረን እንሰራለን ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡ ሺ ጂምፒንግ በበኩላቸው በቻይናና በጀርመን መካከል ያለው ግንኙነት በመከባበርና ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርግ ስርዓት ላይ ተመሰረተ ነው ብለዋል፡፡
ሜርክል በውይይቱ ወቅት አሁን በዓለማችን ያልተለመዱ ለወጦች እየተከሰቱ ይኛሉ፤ አውሮፓም ትልቅ ፈተና ውስጥ ናት ብለዋል፡፡ መራሂተ መንግስቷ በቡድን 20 ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ድሃ ሀገራትን የኮቪድ-19 ክትባት እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት አለብን በማለት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡