አራት ተጠርጣሪዎች ከተሰረቁ የመኪና መለዋወጫዎች ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ::
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 24 ፣ 2013 በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለልማት በተዘጋጁ ቦታዎች ላይ በተደረገ አሰሳ አራት ተጠርጣሪዎችን ከተሰረቁ የመኪና መለዋወጫ እቃዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ክልል ልዩ ቦታ አሜሪካ ግቢ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ነው።
መንግስት ለልማት ብሎ ባዘጋጀቸው ቦታዎች ላይ ግለሰቦቹ በህገ ወጥ መንገድ የሸራ ቤት ወጥረው ለተለያየ ህገ-ወጥ ተግባርና ለወንጀል መሸሸጊያነት በማዋል ከተለያዩ ቦታዎች የሰረቋቸውን የመኪና እቃ መለዋወጫዎች አከማችተው ተገኝተዋልም ነው ያለው፡፡እቃዎቹን በደላላ አማካኝነት በተለምዶ ሶማሌ ተራ እየተባለ ወደሚጠራው አካባቢ በመውሰድ ለሌሎች ግለሰቦች ሲሸጡ እንደነበርም በምርመራ መረጋገጡንም አስታውቋል፡፡
183 ስፖኪዮ፣ 122 የመኪና የፍሬን ጎሚኒ፣ 21 ፍሬቻ ባለመስታወት፣ ሶስት የመኪና ቴፕ፣ 36 የመኪና ቸርኬ ጌጣጌጥ በማስረጃነት ተይዘዋልም ብሏል፡፡
ንብረት የጠፋባቸው ግለሰቦች በወቅቱ ወደ አቅራቢያቸው ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ስለማመልከታቸውና የጠፋባቸውን የእቃ አይነት ማስረጃዎችን ይዘው በመቅረብ ንብረታቸውን መውሰድ እንደሚችሉ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የመርካቶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ገልጿል።