አሸባሪው ህወሓት እንደ አዲስ ከወረራቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲወጣና በቀጠናው የከፈተውን ጦርነት እንዲያቆም የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አሳሰበ።
አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2014 አሸባሪው ህወሓት እንደ አዲስ ከወረራቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲወጣና በቀጠናው የከፈተውን ጦርነት እንዲያቆም የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አሳሰበ።
የክልሉ መንግስት በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ ከሰሞኑ አሸባሪው ቡድን በተደራጀ መልኩ በአብአላ፣ በመጋሌና ኤረብቲ ወረዳዎችን በመቆጣጠር እና በራህሌ ወረዳንም ከፊል ቀበሌዎች ድረስ ዘልቆ
በመግባት ከባድ ጥቃት ከፍቶ ንፁሀንን በመግደል እና በማሳደድ ወረዳዎቹን እያወደመ እንደሚገኝና ከ220 ሺህ በላይ ንጹሃን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀለ የአፋር ክልል አስታውቋል። አሸባሪው ቡድን የራሱን እድሜ ከማራዘም ውጭ ጭራሽ ቅንጣት ታክል ለህዝብ ሰብአዊነት የሚሰማው አለመሆኑን፤ የአፋር ንፁሃንን በመግደልና በማሸበር ብቻ ሳይሆን እየገለፀ ያለው፣ ከትግራይ እናቶች ጉያ መንጥቆ የሚያወጣቸውን በጦርነቱ በማሰለፍ እና በኪልበቲ ረሱ በኩል ለትግራይ ህዝብ ይደርስ
የነበረውን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲስተጓጎል በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈፀምም ነው ብሏል።
አሸባሪው ህወሓት ከአሁን በፊት በአፋር ክልል የበርካታ ወረዳዎችን ወሰን ጥሶ በመግባት በአሰዳ፣ በጋሊኮማ፣ በኡዋ፣ በጭፍራ፣ በሀደሌ ኤላ፣ በደርሳ ጊታ እና ሌሎች አካባቢዎች አሰቃቂ የዘር ማጥፋትን ጨምሮ በርካታ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን የሽብር ቡድኑ ማድረሱን መግለጫው አስታውሷል። ሆኖም ግን ክልሉ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመስራት ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ለአብነት ጠቅሷል።
ቡድኑ ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም እና የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ እየፈጸመ ካለው የሽብር ተግባሩ እንዲወጣ የአለም ማህበረሰብ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት እና የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን የውሸት ማወናበጃ መግለጫዎችን ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመረዳት ይህን ድርጊቱን በቃ እንዲል ጥሪ አቅርቧል። የክልሉ መንግስትም ሆነ የአፋር ህዝብ ለትግራይ ህዝብ በቡድኑ ወረራና ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር የሚሰራ ይሆናልም ብሏል መግለጫው።